ከዘከሪያ መሐመድ
ይህ ታሪካዊ ቀን፣ ለእኔም ታሪካዊ ሆኖ ያልፍ ዘንድ የአንድዬ ፈቃድ ሆነና፣ ዛሬ ሁለት እንግዶች በመኖሪያ ቤቴ አስተናገድሁ፡፡ አንደኛው የጥላሁን ገሠሠ የበኩር ልጅ፣ ምንያህል ጥላሁን ገሠሠ ሲሆን፣ ሌላው የጥላሁንን የሕይወት ታሪክ እጽፍ ዘንድ ያነሳሳኝን የቤተሰብ ታሪክ ማስታወሻ ከ1934 ጀምሮ የጻፉት የአቶ ፈይሣ ኃይሌ 8ኛ ልጅ ሳምሶን ፈይሣ ነበር፡፡ ጀምበር እስክትጠልቅ ድረስ እየተጨዋወትን ቀኑን በግሩም ሁኔታ አሳለፍን፡፡
“ጥላሁን ገሠሠ፡ የሕይወቱ ታሪክና ምሥጢር” የተሰኘውን መጽሐፌን ለምንያህል ከታላቅ አክብሮት ጋር አበረከትሁለት፡፡ እርሱም በደስታ ተቀበለኝ፡፡ የጋሽ ጥላሁንን ባዮግራፊ ለበኩር ልጁ ባበረከትሁበት ቅጽበት፣ ከፊርማዬ በታች መስከረም 17፣ 2008 ብዬ ስጽፍ ልዩ ስሜት ነው የተሰማኝ፡፡ ከምንያህል እና ከሳምሶን ጋር ከዚህ በፊት የያዝናቸው ሁለት ቀጠሮዎች በተለያዩ ምክንያቶች ተስተጓጉለውብናል፡፡ ዛሬ የመጡት ተቀጣጥረን አልነበረም፡፡ የሆነው ሆነና በዕለተ መስቀል፣ በጥላሁን የልደት ቀን ምንያህል እና ሳምሶን ከች አሉ፡፡ በታላቁ ከያኒ የልደት ቀን፣ የበኩር ልጁ ምንያህል ጥላሁን ገሠሠን በመኖሪያ ቤቴ በማስተናገዴ እና በዚሁ ዕለት መጽሐፌን ላበረክትለት በመቻሌ በጣም ደስ ብሎኛል፡፡
‹‹የማያውቁት ሀገር አይናፍቅም
በፍቅር አንቺን ነው ሌላ አላውቅም›› እያለ የዘፈነው ያ የ1970ዎቹ ወጣት ምንያህል ጥላሁን ገሠሠ፣ ምን ያህል እንደተቀየረ አያችሁን?