[ቴዲ ድንቅ – አትላንታ]
ባላገሩ አይድልን በጥቂቱ ካልሆነ በሚገባ አይቼው አላውቅም። ለነገሩ ከአገር ቤት ከሚተላለፈው የድራማ ብዛት ፣ የበዓል ልዩ ዝግጅት ብዛት፣ ከወሬ አቀባዮች ድረገጾች ብዛት፣ ከሶሻል ሚዲያው ብዛት፣ ሁሉንም ባላየው አይፈረድብኝም ።
የመጨረሻውን ማየት ስለፈለኩ ግን አየሁት። ወይ ቀድሞ ብዙ ተወርቶለት ፣ በጣም ተክቧል፣ ወይም ደግሞ እኔ ችግር አለብኝ። ምክንያቱም ፣ ከዚህ በፊት አየነው የሚሉ ጓደኞቼ አድንቀው ስለሚያወሩ በጣም ብዙ ጠብቄም ይሁን አላውቅም የዛሬው የመጨረሻ ዝግጅት አልጣመኝም። የተወራላቸውና ከስንት ሺ ተወዳዳሪዎች መካከል፣ ከሶስት ዓመት አድካሚ ጉዞ በኋላ፣ ምርጥ አስር ሆኑ ተብለው የቀረቡትም (1 እና 2 ከወጡት በቀር) ገና ልምምድ ላይ ያሉ ነው የሚመስሉት።
የ እስከዛሬውን በሚገባ ስላላየሁት ልተወውና ዛሬ ሊስተካከሉ ይችሉ የነበሩትን ልጥቀስ፦
– እንደኔ ግምት አስተዋዋቂዋ ልጅ ድምጽ እንጂ የአቀራረብ ወዝ (ሂዩመር የሚለውን ተርጉሙና አስገቡት) አላየሁባትም። በየመካከሉ ለማዋዛትና ለማጣፈጥ የምትጨምረው ነገር፣ እዚያው ፈጥራ ዘና የምታደርግበት ነገር አላየሁም። የተጻፈውን ብቻ የምታነብ ነው የመሰለኝ።
– ዳኞቹ በበኩላቸው ፣ በየመካከሉ ፣ “ይቅርታ አንድ ጊዜ .. ፣ እዚህ ጋር … ” እያሉ ከአሰተዋዋቂዋ ጋር እየተጋፉ ለመናገር መሞከራቸው ትልቁን ዝግጅት ያኮስሰዋል። አዘጋጆች፣ ዳኞችና የዝግጅቱ ሞተሮች (ከጀርባ ያሉ ፕሮዲውሰሮች [ካሉ] ] በተለየ መነጋገሪያ ሊነጋገሩ ይችሉ ነበር። ወይም ቀድመው ምን ምን መደረግ እንዳለበት በሚገባ መግባባት ነበረባቸው።
– መብራት የሚጠይቅ ዝግጅት ያቀረቡት የቡድን ዳንሰኞች፣ የመብራት ቅንብርና ሃይል፣ እንዲሁም ቴክኖሎጂው ጭምር እንደሚፈልጉት መሆኑን ያረጋገጡ አልመሰለኝም። በመብራት መለዋወጥና መፍካት ሊደምቅ የሚችል ዝግጅታቸው እንደ ደበዘዘ ቀርቷል።
– ዳዊት ጽጌ አንደኛ መውጣቱ ድሮም የተጠበቀ ይመስላል፣ እንዲያውም ከውድድሩ በፊት ጀምሮ ፣ እሱ ራሱ ጭምር ፣ አንደኛ መውጣቱን ያመነበት ይመስላል። ጥሩ ድምጽ እንዳለው ተማምኗል። በርግጥም አለው። እናም የመጨረሻ የሙዚቃ ዝግጅቱን ሊያሸንፍበት ርግጠኛ እንዲሆን የተለየ ዝግጅት፣ አዕምሮ ውስጥ እንዲቀር ጥረት ያደረገ አይመስልም። ተመልካቹም ምንም አዲስ ነገር ያየ አልመሰለኝም፣ እንዲያውም፣ ከመጨረሻው ወሳኝ የዳዊት ጽጌ ሙዚቃ ዝግጅት ይልቅ፣ የጥላሁን ገሠሠ መታሰቢያ ዝግጅት ነው ያስመሰለው።
– ውድድሩ ሶስት ዓመት ሙሉ ሲታይ እንደመቆየቱ መጠን የመጨረሻው ዕለት ዝግጅት ከስከዛሬው ለየት የሚልበት መንገድ የታሰበ አይመስልም። ለምሳሌ በየውድድሩ ጣልቃ፣ እንደ “ሰርፕራይዝ” ቴዲ አፍሮ፣ ወይ አስቴር አወቀ .. ወይ መሃሙድ አህመድ፣ ወይም ሌላ ሙዚቃ እንዲጫወቱ ቢደረግ ጥሩ ነበር የሚል ግምት አለኝ። አለበለዚያ “የመጨረሻ” ከመባሉ በቀር የሁልጊዜ አይነት ውድድር መስሎ ይቀራል።
በአዳራሽ ከቅርብም ይሁን፣ እንደኔ ከሩቅ አገር በቲቪ ያየው ተመልካች “አዲስ ነገር” ያየው “እገሌ አሸነፈ፣ አገሌ ሁለተኛ ወጣ!” የሚባለውን የመጨረሻ ድምጽ እንጂ፣ ከቀረበው ዝግጅት ውስጥ ከሌለው የተለየ ነገር ያየ አይመስለኝም። ምናልባት፣ ሁለት ሁለት ሆነው፣ ወይም ሁሉም ተወዳዳሪዎች በጋራ ለየት ያለ ነገር ይዘው ቢቀርቡ፣ ቢያንስ የሚወራ ነገር ይኖራል። አሁን ግን “ዳዊት ጽጌ” ከማሸነፉ ውጭ፣ እህ ተብሎ የሚወራለት ሌላ ነገር አልከተሰተም።
ዳር ሆኖ መተቸት መቼም ቀላል ነው (እኔ እንዳረኩት) ፣ ግን መቼም ከዚህ የተሻለ አጨራረስ እንዲኖር ከመመኘት ነው። አሸናፊ ሆኖ የጨረሰውን ዳዊት ጽጌ እንኳን ደስ አለህ እላለሁ። እንኳን ሶስት ዓመት አይደለም፣ እኛ የሶስት ሰአት የአዳራሽ ዝግጅት ለማዘጋጀት የምንደክመውን ስለማውቅ፣ ጽናት፣ ቁርጠኝነት፣ ራዕይ፣ ግብ፣ ጠንካራ መንፈስ፣ ትዕግስት፣ ትህትና፣ ብዙ ጨጓራና (በብስጭት እንዳይቃጠል)፣ ተራራ የሚያክል ትከሻ (ሁሉን እንዲችል) የተሰጠውን ጓደኛችን አብርሃም ወልዴ እንኳን ለዚህ ቀን አበቃህ፣ ከወገብ ህመምህን ፈጣን ፈውስን ታገኝ ዘንድ ምኞቴ ነው።