Quantcast
Channel: ዘ-ሐበሻ – Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 8745

ዮ ..ሀ.. ማስቃላ!! ….አደይ ሲፈንዳ!! (አስፋ ጫቦ )

$
0
0

አስፋ ጫቦ Corpus Christi, Texas USA

መስከረም ሲጠባ ፤አደይ ሲፈንዳ፤

እንኳን ሰው ዘመዱን

ይፈልጋል ባዳ ማለት እውነት ነው!ለኔ፣የኔ እወነት ነው!

አቶ አሰፋ ጫቦ

አቶ አሰፋ ጫቦ

ዳዊት “..ወምድርኒ ትገብር ፋሲካ …፤ሰማያት ደስ ይበላቸው፤ምድርም ሐሴት ታደርግ“  ያለው መሆኑ ነው።ዘፈን ዘፈን !ዝፈን ዝፈን! ብሎኛል እንደማለት ።ዳዊት የተናገረው በምናቡ ኢትዮጵያን እያየ መሆን አለበት። እንጅማ የሱ አገር በአበባ ሠምሮ፥ደምቆ፥ ሰውም፤ምድሪቱም የሚዘፍኑበት አይመስለኝም:: የሰሐራ በረሀ ቅጣይ  መሆኑ አይደል!! “ማርና ወተት የሚፈስባትን ቅድስት ሀገር” ለመሳለም ሔዶ የተመለሰው ኢትዮጵያዊ ቅድስትነቱ እንኳን ይሁን ማርና ወተት የሚፈስባትስ የኔይቱ አገር ነች” አለ። አለ ብሏል ብሎ ዶናልድ ለቪን (Donald Levin Greater Ethiopia) እንደሚጽፈው ለማለት ነው።እንዲያ ብሎ ጽፎ ያነበብኩ ይመስለኛል

መስከረም በጠባ፤አደይ በፈንዳ ቁጥር ያለፈውን ስንትስ አመት በመንፈስ ትዝታ  ወደጥንት፤ወደልጅነቴተ ይዞኝ ጭልጥ ይላል።ከዚህ ውስጥ ሶስቱ  ጎልተው፤ፍክተው ፤ፋፍተው ይመጡብኛል። የመጀመሪያው የዕንቁጣጣሽ ለት ጎህ ሲቀድ የጨንቻ ገብርኤል ቅዳሴ ማሕሌትና የትንሣኤ(ፉሲካ)ሌሊት ሲሆን ሁለተኛው የጋሞ ማስቃላ፤በተለይም የዶርዜ ማስቃላ፤በተለይም ዶርዜ ላካ የሚከበረው ነው።

መስከረም 1 ጥዋት ድርቡጭ ያለች ጎጆ የሚያክል ስንዴ ይከመርና በዚያ ላይ ካህኑ ወይ መርጌታው የዚያን አመት በአላቱና አጽዋማቱ የሚውሉበትን ቀን ያውጃል። በአዋጁ ውስጥ የዘመን አመጣጥን፤የዘመን አቆጣጠርን ከአዳም አስከዚያ ለት የተርተራል::የዘክራል።         በአላቱና አጽዋማቱ የሚዉሉበትን ቀንና ምክንያትም ሲደረደር አብቅቴና መጥቅ የሚለውም አለው። “አብቅቴ ሲበዛ መስከርምን ንዛ ፤አብቅቴ ሲያንናስ ጥቅምትን ዳስ!” የሚለው አለው። አብቅቴ ፤መጥቅ ፤ንዛ፤ዳስ ምን እንደሆነ ያኔም አሁንም አልገባኝም። ስለዘመናት አቆጣጠር ዶክተር ጌታቸው ኃይሌ የተረጎመውን መጽሐፍ ያነበብኩ ይመስለኛል። ማንበብ ማለት መረዳት ማለት አይመስለኝም። ያም ሆኑ ትእይንቱ የሚፈጥረው፣የራሱ፣ ነፍስን ፣ መንፈስን ወደላይ አውጥቶ የማንሳፈፍ ባሕርይ ስለአለው ያው ከኔው ጋር ቀርቶ ትዝታ የሚሉትን ሆኗል።

እኔው እኔን ከሆንኩ ወዲህ (ቶሎ ይመስለኛል እኔ እኔን የሆንኩት) አስገዳጅ ምክንያት ካልተገኘ በስተቀር ቤተክርስቲያን ሔጄ የማውቅ አይመስለኝም።ከዚያ ውስጥ ለሁለት ይሁን ሶስት አመት ለፋሲካ ያደርግነውን አሁን ይህንን መጻፍ ስጀምር አስታወስኩት። ህግ ትምህርት ቤት ( Faculty of Law)እያለሁ፤መልአከ ድንግል እንግዳየሁ የሚባል፤ ጎንደሬ፤ የቤተ መንግስቱ ቅዱስ ገብርኤል ይሁን ባህታ ዲያቆን የነበረ ጓደኛ ነበረኝ። መልአከ አሁን ከኛ ተለይቷል። ቅዳሜ ስሁር፤አራት ኪሎ፤አልማዝ ክፍሌ ቡና ቤት የሚደረገውን ሁሉ እያደርግን እናመሽና ወደአራት ሰአት ተኩል ቤተክርስቲያን ሔደን ስነስረአቱ ከተፈጸመ በኋላ ወደምንሔድበት እንሔድ ነበር። ከአልማዝ ቡና ቤት በእገር የ10 ደቂቃ መንገድ ቢሆን ነው።

በኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን፤የትንሳኤ በአል ትናንትንና ዛሬ ቁልጭ ብለው የሚለየበት በአል( ቀን)ይመስለኛል።ለ56 ቀናት ጾም ነው። ጾም ማለት ደግሞ ከማንናቸውም የእንስሳትና አእዋፋት አስተውጸኦ መታቀብ ማለት ነው።ከዚህም ሌላ አድማቂ የሚሆኑት ከበሮ፤መቋሚያ ፤ጽናጽል የመሳሰሉት ሁሉ  እርፍት ይወስዳሉ።ድምጻቸው አይሰማም።ይጾማሉ እንደማለት!!  ከሶስቱ ዜማ አይነቶች፤ግዕዝ፤እዝልና ራራይ ግእዝ ብቻ ነው የሚዘመረው። የሆነ የትካዜ ቅላጼ( Subdued) አለው ተብሎ ይሆናል። ልክ ከለሊቱ 6 ሲሆን፤” ክርስቶስ ተንሰአ እሙታን ፤በአቢይ ኃይል ወስልጣን፤አስሮ ለሰይጣን አግአዞ ለአዳም”  ከተባለ በኋላ ምስባኩም “ክርስቶስ ተንስአ እሙታን፤ሞተ ወኬዶ ለሞት…” የሚለው ነው:: እኒያ ሲጾሙ የሰነበቱት ማድመቂያ መሳሪያዎች ስራቸውን  ሲጀምሩ እውነትም ፋሲካ፣እውነትም ትንሳኤ በል! በል!  የሚያሰኝ መንፈስ ይሰፍናል።ያንን መካፈል መንፈሴንም ስጋዬንም የሚያድሰው ይመስለኛል። የእርካታ ምንጫ ብዙ ነው። ሁሉንም በቅጡ ለየተን የምናውቅ አይመስለኝም። ሲመጣ ግን መለየት መቻሉ መታደል ይመስለኛል።

ሌላው አደይ ሲፈንዳ የሚታውሰኝ ጨንቻ ነው።አሁን ሳስበው እንደ ጨንቻ         የአደይ አበባ ፍንዳታ ገኖሮ፣ አጥለቅልቆ፣ሠምሮ፣ፈክቶ የሚታይበት የትም ወደየትምም ያለ አይመስለኝም:: Perception is Reality ይላሉና በልጅነት አንዴ የታተመው ምናልባት ሌላ አላይም ብሎም ሊህን ይችላል ብሎ መጠርጠርም የሚቻል ይመስለኛል።

አራዳ ሲቀር (አራዳማ አራዳ! ነውና ) የቀረው፣ነፍጠኛ ፤አየለ፤ ማርያም፤ ገብርኤል፤ መድኃኔ ዓለም ሠፈር፤ካቡራ፣ጥቅጥቅ፣ችምችም ያለ የአደይ አበባ ጫካ ይሆናል።ለኔ ከአበባነቱ ይልቅ አስቸጋሪነቱ ነበር ጎልቶ የሚታየኝ። ጎሮቤት ተልኮ መሔድ፤ውሐ ለመቅዳት ጨፌ መውረድ፤በየእሁዱና በአላት የሆኑ ለት ገብርኤል ሰፈር መሔድ ራሱን የቻለ ጤዛ -በጤዛ የሆነ የሳር፤የአበባ ጫካ ወይ እያባበሉ ወይ እየራሱ መጓዝ ራሱን የቻለ ፈተና እንደነበረ ፍንትው ብሎ  ዛሬም ይታየኛል። ልጃገርዶች ከዶኮ መጥተው ለከብቶቻቸው ያጨዱ እንደሁ እስኪተካ ትንሽ ትንፋሽ ይገኛል። ጨንቻ የትና- የት ሰፊ ከተማ ስለሆነ ሁሉን አይዳርሱት ነገር! የኛ ቤት ለዶኮ ቀረብ ስልሚል ከዚህ እድል በመጠኑ የኛ ሰፈር ተጠቃሚ ነበር። ዶኮ ማለት ከጨንቻ ወደምእራብ ያለው አገር ነው። ዶርዜ ወደደቡብ ነው። ዶርዜዎች ግን መጥተው ሲያጭዱ አላየሁም::

A Thousand Suns | Global Oneness Project

አሁን ወደ ሌላው የልጅነት ትዝታዬ፣ወደጋሞ ማስቃላ እሔዳለሁ።የጋሞ ማስቃላ አናቱ መስከረም 16 ወይም 17 ወይም ያው የቀረው የኢትዮጵያ የመስቀል በአል (ደመራ) ሲከበረ ነው።የጋሞ ማስቃላ ምንደነው? ጋሞ፣ ማስቃላ በሚለው፣ ምንን ፣ ማንን ነው የሚያከበረው? የጋሞ አዲስ አመት መሆኑ ነው? የጋሞ አዲስ መንግስት ሥልጣን የሚረከብበት ቀን ነው? በጋሞ በዚያ አመት የተጋቡ ሙሹሮች፤የወጣትነት ዘመናቸው አልፎ ወደ ሙሉ ሰውነት የተሸጋገሩበትን ቀን የሚያስመርቁበት፣የሚያዉጁበትን ቀን ነው? በዚያ አመት የተገረዘ ሁሉ የተገረዘ መሆኑ ባደባባይ የሚነግርበት ቀን ነው? ሌላም ሌላም!

ለመሆኑ የጋሞ ማስቃላ ወይ አዲስ አመት ወይም አዲስ መንግስት ወይም በሆነ ሌላ ስም  የሚታወቅበት  ቀን ነው? የተጠና፤ቢያንስ እኔ የማውቀው ጥናት ስለሌለ በልጅነት ያስተዋልኩትንና ከዚያም ሊሆን ይችላል የምለውን ነዉ እዚህ ለማቅረብ የምሞክረው።

የጋሞ አዲስ አመት ዝግጅት የሚጀመረው(ለዚህ ውይይት እንዲረዳን አዲስ አመት እንበለውና) ወይ በሰኔ ወይም ሐምሌ ነው። ለዚያ ምልክቱ የግጦሽ ምሬት እንዳለ ይከለልና (ካሎ ነው የሚባለው) መሐሉ አንድ ረዥም አንጨት ይተከላል። ይህ “እዚህ ከበት ድርሽ እንዳይል!” የሚል አዋጅ መሆኑ ነው። ድርሽም አይልም!! ለጋሞ እረኛ አስቸጋሪው ወቅት ይሕ ይመስለኛል። ባንድ በኩል የምህር እርሻ ይጀመራል።በሌላ በኩል የተለመደው የከብቶች የግጦሽ ቦታ ተከልክሏል። ከብቶች ደግሞ በልተው ጠገበው መመለስ አለባቸው። ያንን ሟሟላት የረኛው እጣው ፋንታው ይሆነል።ማለት የፈለኩት በመጠኑ ግልጽ የሆነ ይመስለኛል።

የጋሞ መንግሥስት በየአመቱ በምርጫ የሚመጣ ነው። ተመራጩ ሁዱጋ ወይም ሐላቃ ይባላል።ወደ አርባ የሚደርስ አገር( ደሬ)ስለአለ አንዱ ባንዱ ሌላው በሌላው ይጠራል። የልዩነቱን ምክንያት አላውቅም።የዶርዜው ሐላቃ ነው የሚባለው። የሥልጣን ዘመኑም         በአብዛኛው አንድ አመት ሲሆን ሁለት አመት የሚሆንበትም ደሬዎችም አሉ።ጋሞ የነገስታት (ካዎ) አገር ነው። ካዎው (ንጉስ)ምልክት እንጅ ስልጣን የለውም።አልነበረውም ማለት የሚሻል ይመስለናኛል! ከምንሊክ ወዲህ ባላባት የሚል ስም ተስጥቷው ከግራዝማች እስከ ፊታውራሪ ደርሰው የአጼው መንግስት በዝቅተኛው ደርጃ አካልና አስፈጻሚ ሆነዋል። በዚህ ሳቢያ በባህሉ ያልነበራቸውን ስልጣን ያገኙ ይመስለኛል።

ይኸ ነገር ካሰብኩት በላይ የተንዛዛብኝ መሰለኝ። አንድ በደንብ ያላጠናሁት ግን የሚከነክነኝ ነገር አለና ትንሽ ልሞክረው። ጋሞ በአመት ውስጥ  የሚያከብረው አንድ፣ብቸኛ፣ ሁለገብ፤ ሁለነክ በአል አለዉ።ይህም ማስቃላ ነው። ለመሆኑ የማስቃላ አከባበር ጊዜውወቅቱ ከመቼ እስከመቼ ነው? ከፍ ብዬ መጥቀስ እንደሞከርኩት ካሎ  (ግጡሽ መሬት ላይ ማእቀብ) በሰኔ ወይም ሐምሌ የሚጀምር ይመስለኛል። የሚደመደመው ወደመስከረም መጨረሻ ገደማ ነው። አናንቱን፣ጣሪያዉን የሚነካው መስከረም 16 ወይም17 ነው። በዚህ የ3 ወራት ጊዜ ድምቀቱ እንደ^ ይሆናል።በሰኔ ወይም ሐህምሌ ከአንደኛው ጫፍ በወጣቶች የየሰአት በኋላ ዘፍን ታጅቦ ይጀምርና ቁጥሩም እድሜዉም እየጨመረ ይሔድና ጣሪያውን የማስቃላ ለት ይረግጣል። ልክ ጅምሩ ላይ እያሻቀብ እንደሔደው ሁሉ እያሽቆለቆለ ይሔድና መስከረም ሲገባደድ ያጠናቀቃል።

የክረምቱ ወራት የእርሻ፤የመዝራት፤የኩትኳቶ፣ ጥቢው ደግሞ የእሸት ወራት ነው። በጥንት የመካከለናኛው ምስራቅ ታሪክ ይህንን ወራት የአምልኮ ወራት ያደርጉታል። የምርት አማል ክትን (Gods of Fertility) የሚያመልኩበት፤ከደረሰው አዝመራ መስዋእት የሚያቀርቡበት ነው።ሁለመናው ሲታይ የጋሞ ማስቃላም የምርት አምላክን  ማወደሻ ይመስለኛል። ከሆነ ደግሞ ይህንን የሚከተል የተረፈ ቢኖር ጋሞ ብቻ ሊሆን ነው። መካከለናኛው ምስራቅ  በክርስትናና እስልምና በአብዛኛው ተተክቷል። አሁን ኦሪትን ጠጋ ብለን ብናነበው አብዛኛናው  በአላትና መስዋእት  ከምርት ወጤት ጋር የተገናኙ ናቸው። ማስቃላ መስቀል ከሚለው ከክርስቲያኑ  ነው የመጣው? ሊሆንም ላይሆንም ይችላል። ከሆነ ደግሞ ማን ከመን ወሰደው የሚለው ለአጥኒዎች የሚተው ይመስለኛል።

በመጨረሻም ከሶስቱ የልጅነት ትዝታዬ አንዱ ወደሆነው ወደጋሞ ማስቃላ፤በተለይም የዶርዜው ማስቃላ፤በተለይም ወደዶርዜ ላካ ማስቃላ አከባበር እሔዳለሁ። ዶርዜ ላካ ከጨንቻ፤በልጅ እግር ከ30 እስከ 45 ደቂቃ ቢወስድ ነው። ማንኛውም የጋሞ ደሬ የሕዝብ አደባባዮች አሉት። ከዚህ ዋንኛው በሁዱጋው ወይም በሐላቃው ሰብሳቢነት(ሊቀመነበርነት) የሚስበሰቡበት ታላቁ ነው። ከትልልቅ ዋርካዎችና ሌሎችም ዛፎች ስር ነው።ጥርብም ከሚመሳስሉ ደንጊያዎች የተሰራ፣መደገፊያ ጭምር ያላቸው መቀመጫዎች አሉት። ሁሌም ሜዳማ ቦታ ላይ ነው። ብዙ ጊዜ ሜዳው ገበያና የባሌ (ሙሾ ማወረጃ)ማረገጃ ጭምር ነው። ላካ ይኸ ሁሉ አለው። ለባሌው (ሙሾዉ) የጸጋዬ ገብረ መድሕንን ሞትም ይሙት ማንበብ ድምቀቱን የተሻለ የሚገልጸው ይመስለኛል።

አዲስ አበባ፤ጃን ሜዳን የጥምቀት ለት በአይነ ሒሊና ማየት የማስቃላ ለት ዶርዜ ላካን የተሻለ የሚገልጸው ይመስለኛል። የክብር እንግዶቹ፤ለክብራቸው በተዘጋጀው ስፍራ (መቀመጫ) የሰየማሉ። ያለፈው አመት ሁዱጋ ወይም ሐላቃና  አዲሱ ተመራጭ ጎን ለጎን ይሰየማሉ። ባለፈው አመት የተዳሩ ሙሹሮች፤ባለፈው አመት የተገረዙ ወንዶችም እንዲሁ በተመደበላቸው የክብር ቦታ ይሰየማሉ። ዘፈን፤ጭፍራ ቀኑንሙሉይወርዳል። ይቀልጣል! ማለት ይሻላል። ቀን ሙሉ ከሚውል የዘፈን ድግስ በኋላ ለዘመኑ የተመረጡት ሥልጣናቸውን ይረከባሉኩ።አዲሱ የዶርዜ መንግስት ተቋቋመ፤ስራውንም ጀመረ ማለት ነው።ይኸው ትእይነት ጋሞ ደሬዎች ሁሉ ይፈጸማል። ሙሹሮቹ ተመርቀው ወደ ሙሉ፤ የሕብረተሰቡ አባልነት ተሸጋገሩ ማለት ነው። እኔም ቀኑ፤ ሰአቱ ሳይታወቀኝ በኖ-ተኖ፤ረክቼ ወደጨንቻ የመልስ ጉዞ እጀምራለሁ። ሁለት ሰአት ያክል የሚወስድብን ይመስለኛል። የምናውቀው ጨንቻ ስለሆነ ለመድረስ የሚያጣድፍ ነገር ይለምና!!

እንኳን ሰው ዘመዱን ይፈልጋል ባዳ !!ነው የተባለው? ተርፎን ለባእድ ጭምር የምንቸረው ምርት የሚሰጥ አመት ያድርግልን

 ዮ….ሐ ማስቃላ!! መስከረም ጠባዬ!!

 


Viewing all articles
Browse latest Browse all 8745

Trending Articles



<script src="https://jsc.adskeeper.com/r/s/rssing.com.1596347.js" async> </script>