ኢትዮጵያውያን ዛሬ ላሉብን ችግሮች ጅማሮው ትናንት ህውሃት ስልጣን ከያዘ ጀምሮ የመነጩ ናቸው የሚል መደምደምያ ላይ የሚያደርሰን አመክንዮ ያለ አይመስለኝም። ያ ከሆነ ዘንድ ከዛም ቀደም ሲል ችግሮቹ ነበሩ ወደ ሚል ይወስደናል። ታድያ እዚህ መሰረታዊ ሃሳብ ላይ ከተስማማን ደግሞ ችግሮቻችን ምን ምን ነበሩ ወደ ሚሉት ዝርዝር ጉዳዮች በሂደት ያሸጋግረናል ማለት ነው። ይህን ተከትሎ ችግሮቻችንን በመቅረፍ ላይ መተማመን መድረስ ሌላኛው ሂደት ነው። በዛም አያበቃም ቀጣዩ እርምጃ በጋራ ተሳስበን እና ተከባብረን ልንኖርባት ስለምናስባት የጋራ ሃገር የጋራ የሆኑ እሴቶቻችንን ልናጎለብትባቸው የሚያስችሉንን የጋራ መድረኮች ልንፈጥር ግድ ይላል ማለት ነው። እናስተውል。。 የጋራ ቤታችንን ለመገንባት በሚያስችለን ጉዳይ ላይ የጋራ መወያያ መድረክ እና መድረኮች ነው ያልኩት።
እነዚህ የጋራ መድረኮቻችን ደግሞ የፖለቲካው ፣ የስፖርቱ ስብስቦች ፣ የባህል ስብስቦች እና ኤግዝቢሽኖች ወዘተ ተብለው ሊዘረዘሩ ይችላሉ። እነዚህ የእምነት ፣ የብሄር ፣ የቋንቋ ፣ የፆታ እና ሌሎች የአመለካከት ልዩነቶች ጨምሮ እንደተጠበቁ ሆነው በኢትዮጵያዊነት ብቻ ዜጎች ሚስተናገዱባቸው ሊሆኑ ይገባል። እነዚህ ስፍራዎች ደግሞ አግላይ ሳይሆኑ አቀራራቢ ፣ ሚጎረብጡ ሳይሆኑ የተደላደሉ ሊሆኑ ሚገባቸው ቦታዎች ናቸው። እኩልነቱ ከአንደበት አልፎ በውስጣችን ከሰረፀ ማለት ነው። ታድያ እነዚህ ከየትኛውም አድሏዊ አስተሳሰቦች ፣ መገለጫዎች ፣ መንፈሶች ፣ እና በተግባር ከሚገለፁ ጉዳዮች ሁሉ በተቻለ መጠን የፀዱ ሲሆኑ ነው። በዋነኝነት መፍትሄው ደግሞ የእኩል ተሳታፊነት እና አሳታፊነት ሚዛናቸው ሲጠበቅ እና ግልፅነት ሲታከልባቸው ነው። ከየአቅጣጫው አንድነት አንድነት ሲባል በተደጋጋሚ ይነገራል። አንድነት ማለት ምን ማለት ነው? አንድነት ስንል ተመሳሳይነት ማለት ነውን ? አንድነት ለምን ያስፈልጋል ? አንድነት በምን ላይ ? 。。。ወዘተ ዝርዝር ሃሳቦች ሊነሱ ይችሉ ይሆናል። ሆኖም ዛሬ ግን በነዚህ ዝርዝር ጉዳዮች ላይ ረዥም እና አሰልቺ የሆነ ፅሁፍ ከማስነብባቹ በይደር ትቼ ወደ ዋና የተነሳሁበት መልእክት በአቋራጭ ሃሳቡን መንደርደርያ አድርጌው ልግባ። ብዙ ግዜ አንድነት ስንል ተመሳሳይነት ማለት እንዳልሆነ ልብ ልንል ይገባል። ሰዎች በዘር ፣ በቋንቋ ፣ በሃይማኖት ፣ በፆታ ፣ በመደብ ደረጃ፣ በቀለም እና አካባቢ ወዘተ ቢለያዩም ማሳረግያው የሰው ልጆች ነን አንድ ነን የሚለው ነው። ይህ ጠቅል የወል መጠርያ ሰው የሚለው ቃል ወደ ሃገርም ሲመጣ ሁላችንም ኢትዮጵያውያን ነን ወደ ሚለው ወደ አንድ የወል መጠርያ ሊያደርሰን ይችል ይሆናል። ይህ ማለት የተለያየን አይደለንም የሚል የተዛባ አስተሳሰብን ሊያጭር አይገባውም። ኦሮሞ ኢትዮጵያዊ ፣ ከምባታ ኢትዮጵያዊ ፣ ሃድያ ኢትዮጵያዊ ፣ ስልጤ ፣ አፋር ፣ ትግሬ ፣ ጉራጌ ፣ ሲዳማ ፣ ቀቤና ፣ ሶማሌ ፣ አማራ ኢትዮጵያዊ 。。。 ወዘተ በሚል ሌላ የቡድን መጠርያ ደግሞ የተላበስን ነን። በደርግ ግዜ የወጣቶች ማህበር ፣ የሴቶች ማህበር ፣ የጡረተኞች ማህበር የሚሉ ነበሩ። እነዚህ ማህበራት ያስፈለጉበት አብይ ምክንያት እነዚህ አካላት በጥቅል የወል መጠርያቸው ሰው በሚለው ወይም ደግሞ በሌላኛው መጠርያቸው ኢትዮጵያዊ በሚለው ሊጠቃለሉ ባስፈለገ ነበር። ነገር ግን ወንዶች ከሴቶች ያሏቸው ፍላጎቶች ስለሚለዩ። ወጣቶች እድምያቸው ከገፉ አዛውንቶች ፍላጎቶቻቸው ስለሚለይ ወዘተ ነው። ስለሆነም በኛ በሚሉት ስር በመደራጀት ፍላጎቶቻቸውን ይፈፅማሉ ወይም ያሟላሉ ማለት ነው። ማንነትን የዘነጋ ሁላችንንም እንደ አንድ አድርጎ የሚወስድ የአስተሳሰብ ዝንባሌ እየጎላ ከመጣ ለምናልመው አንድነት ከፍተኛ የሆነ አሉታዊ ተፅእኖ ይፈጥራል። የሌሎችን ማንነት እየደፈጠጠ የራሱን ማንነት እያጎላ የሚመጣው አስተሳሰብ በብዙዎች ዘንድ ተቀባይ የመሆን እድሉ የመነመነ ነው። ይህ ደግሞ ለምናልመው አንድነት ጋሬጣ በመሆን ሁሉም የየራሱን ፅንፍ ይዞ እንዲገለል ያረጋል። ዛሬ ዛሬማ አንዳንዶቻችን በመድረኮች እና ስብስቦች ላይ ሁሉ የመታደም ፍላጎቶቻችን ከእለት ወደ እለት እየሞቱ እንዲመጡ እየተደረጉ ይመስላል። ለዚህም አንዱ ምክንያት ሆኖ የሚታየው የአንድ ወገን የቆየ ወግ እና ልማድ አጉልቶ ለማሳየት በሚደረግ በሚመስል እሽቅድድም ውስጥ ግንባር ቀደም መሪነቱን ዳግም እንዲያንሰራራ የመመኘት ሂደት ስለሚንፀባረቅበት ነው። እርግጥ ነው ሃገራችን የሲሶ መንግስት ከነበረችው ቤተ-ክርስትያን ከተገነጠለች የ40 አመታት እድሜ ብቻ ነው ያስቆጠረችው። ቢሆንም ዓለም እየተጓዘበት ያለበትን የሴኩላር አስተሳሰብ ፍጥነት መከተል ጀምርያለሁ ካለችም ያው እሩብ ክፍለ ዘመን ቢሞላም ገና ከራሳችን ጋር የተዋሀዳ አይመስልም። ሆኖም ግን ይህ የሴኩላር አስተሳሰብ መሰረታዊ ፅንሰ ሃሳብ ሃይማኖት እና መንግስት የተለያዩ ናቸው የሚለው ነው።
መንግስት በእምነት ጣልቃ አይገባም እምነትም በመንግስት አሰራር ጣልቃ አይገባም ሲሆን የመንግስት መዋቅር ውስጥ ያሉ ግለሰቦች እምነት አልባ ይሆናሉ ማለትን አያሳይም። ሌላኛው ገፅታው ደግሞ የአንድ ሃገር ዜጎች ከነሱ የተለዩ እምነት ያላቸውን ዜጎች እምነት ፣ ባህል እና ወግ አክብረው እና እውቅና ሰጥተው በመከባበር ላይ መኖር ሲችሉ ነው። መንግስት ከሚያረቃቸው ህጎች በተሻለ ዜጎች በሚያጎለብቷቸው የመቻቻል ባህሎች ሰላም የተሻለ ዘላቂ ነው። ይህ መሰረታዊ የሴኩላር ህሳቤ እንደ ኢትዮጵያ የሃይማኖቶች ብዝሃነት ባሉባቸው ሃገራት ውስጥ ብቸኛው ዴሞክራስያዊ የመንግስት መዋቅር መፍጠር የሚያስችል የተሻለ መንገድ ነው የሚል እምነት አለኝ። ይህ ማለት ታድያ ሰዎች እምነት አልባ ብቻ ሆነው ወደ ፖለቲካ መድረኮች ይግቡ የሚል እንዳልሆነ ልብ ሊባል እወዳለሁ።
እንደ ኢህአዲግ / ህውሃት የተለያዩ ሳንቃዎችን በመደንቀር ሙስሊሙን ዛሬ ከፖለቲካ እንደሚያገለው ሁሉ አንዳንድ የፖለቲካ መድረኮችም ሂድ አትበለው እንዲሄድ አድርገው ብሂልን በመከተል የመግፋት ስራ ሲሰሩ የምናስታውስበት ግዜ እሩቅ አልነበረም ዛሬም እያገረሸ ይመስላል። የልብ መሻከር እንዳይኖር እና በእምነታችን ተከባብረን እንድንዘልቅ የፖለቲካ እና ሌሎች ማህበራዊ ስብስቦች እንደ ስፖርት በአላት ወዘተ ከቤተ እምነቶች ሰበካ ፣ መንዙማ እና ቅዳሴ ማፅዳት ያስፈልጋል። ስብስቦቻችን በነሱ ባይባረኩ ምንም የሚጎላቸው ነገር አይኖርም። ተባርከውም የተጨመረ ነገር የለም ። በመባረካቸውም ሳብያ ከጭቅጭቅ አልዳንም ፣ ልዩነቶችን ከማጉላት አልተቆጠብንም ፣ ፍትህ እና ሰላምም አልሰፈነም። ስለሆነም መድረኮቻችንን የሰበካ እና የቤተ እምነቶች ግቢ ከሚያስመስላቸው አሰራር ማፅዳት ያስፈልጋል ባይ ነኝ። ሰሞኑን ያጋጠመኝ አንድ ክስተት ይህን አምርሬ እንድቃወም ምክንያት ሆኖኛል። በስዊዘርላንድ በምትገኝ አንድ ከተማ በተደረገ ስብስብ ላይ ተገኝቼ ነበር። ስብስቡ ለኢትዮጵያውያን በሃገር ጉዳይ ላይ ፖለቲካዊ ንቃተ-ህሊና(political awareness)ን የማጎልበት እና የመፍጠር ዘመቻ ላይ ያተኮረ ነበር። በሂደቱ እንደ አንድ የመድረክ ተጋባዥ(Panellist)ሆኜ ቀርቤ ነበር። የውይይት ርእስ ይሆናል ተብሎ የተነገረኝ ጉዳይ “የእምነት ተቋማት በመብት ዙርያ ሊኖራቸው ስለሚገባ ድርሻ” በሚል ሃሳብ ላይ ያጠነጠነ ነበር። በትክክል ቃል-በቃል አላስቀመጥኩት ይሆናል። በዚህም ስብሰባ እኔ የእስልምና እምነት ተከታይ እንጂ የሃይማኖት አባት /ሸህ አይደለሁም ብዬ ለጋባዦቼ ምላሽ ሰጠሁ። እንደ እምነት አዋቂ ሆኜ እንዳማልናገር አስረገጥኩ። ሆኖም እንደ እምነቱ አማኝ ሆኜ ግን በፖለቲካ እና ሰብአዊ መብቶች ጉዳይ ላይ እንደሚጨነቅ አንድ ኢትዮጵያዊ አክቲቪስት ልቀርብ እችላለሁ በሚል ፈቃደኛ ሆኜ ቀረብኩ። መድረኩን ያዘጋጁት ወጣቶች ቀናኢነት እና ያላቸው ቁርጠኝነት እንዲሁም መስተንግዶው ይህ ነው ተብሎ በቃላት የሚገለፀ አይደለም።
እንዲሁ ግሩም ነበር ብቻ ባይበቃውም 。。እንለፈው። የነዚህ ወጣቶች አላማ ግልፅ እና ግልፅ ለመሆኑ አያጠራጥርም። ሆኖም በተለያዩ መድረኮች ላይ ጎልተው እንደሚወጡት ሁሉ መድረኮቹን በቅዳሴ መጀመር ብቻ ሳይበቃ ቤቱን ሁሉ በመዝሙር ወደ ቤተ-እምነትነት የለወጡት የእምነት አባት ግን እጅግ አሳዝኖኛል። በእርግጥ ብዙ ክርስትያኖችም ደውለውልኝ ማዘናቸውን ሳይሸሽጉ የገለፁልኝም አሉ። ቀርቦላቸው የነበረው ጥያቄ ሌላ ሆኖ እርሳቸው ያደረጉት ሰበካ እና ዝማሬ እኔ ፈጣሪ አለ ብዬ ማምነውን እንዲህ ካበሸቀኝ ፈጣሪ የለም ብሎ ከኔ እና እኔን ከመሰሉ አማኞች ጋር በጋራ እንወያይ/እንምከር ብሎ የመጣው እምነት አልባው ኢትዮጵያዊ እንዴት እንደሚበግን አሰብኩት። ይህ እኔ በግሌ የታዘብኩት ሂደት ግን አዲስ ክስተት አይደለም። ”የኛው ኢሳት የህዝብ ጆሮና አይን“ በየሄደበት መድረክ ሁሉ አስባርኮ እና አስቀድሶ የሚያስከፍተው ዝግጅቱ ሁሉም የሚያውቀው እውነታ ነው።
በአውስትራልያ የተለያዩ ግዛቶች ፣ የካናዳው ሰልፍ ፣ ሰሞኑን በአማራ እና ኦሮሞው ክልል በህውሃት ጥይት ለተጎዱ ተጎጂዎች በተደረገ የእርዳታ ማሰባሰብያ ጥሪ ፕሮግራሞች ያው ተመሳሳይ ሂደቶች ናቸው። ግን ለምን እስከ መቼ ? እዚህ ጋር ግልፅ ላረገው ምፈልገው ተቃውሞዬ እነዚህ እምነቶች መስጅድ እና ቤተ ክርስትያን አለላቸው እዛ ይስበኩ ነው። እኔ የተለየ እምነት ያለኝን ኢትዮጵያዊ ከኔ የተለየ እምነት ካለው ኢትዮጵያዊ ጋር ብሎም ከማያምነውም ጋር የምገናኝበት ነጻ መድረክ ነው ልቀቁልን የሚል ጥሪ ነው። የወል ጉዳዮች አሉን ስለሆነም እነዛን በነጻነት እና የኔም የሱም ሌሎች መገለጫዎች እሽቅድድም ውስጥ ሳይገቡ በገለልተኛ ቦታ ላይ በነጻነት እናውራበት እንጂ የሃይማኖቶችን ቃኖና ከመቃረን ጋር እንዳልሆነ ልብ በሉልኝ። በተመሳሳይ ሁኔታ ሰሞኑን በቪዥን ኢትዮጵያ እና ኢሳት ዙርያም የተነሳው አነጋጋሪ ጉዳይም ተመሳሳይ ነው። ምን አልባት አንዳንድ ሰዎች ጉዳዩን በማጠፍ ስብስቡ የሃይማኖት አይደለም የሃገር ጉዳይ ነው ወዘተ በሚል ቁንፅል እውቀት የሰሞኑን ቁጣ ሊያጠለሹት ይሞክሩ ይሆናል። መጠኑ ላይ ልንነጋገር እንችል ይሆናል ነገር ግን ጉዳዩ አዋራ ማስነሳቱ አግባብነት ያለው ነው የሚል እምነት አለኝ። ከዚህ ቀደም በተደረገው የቪዥን ኢትዮጵያ ሁለተኛው ዙር ስብሰባ ላይ ተመሳሳይ ወቀሳዎች አልተነሱም ነበር። ዛሬ ለምን? የሚለውን ጥያቄ መጠየቅ አግባብነት ያለው ይመስለኛል። ፕሮፌሰር መሳይ ከበደ በባለፈው ማርች በተደረገው የቪዥን ኢትዮጵያ ስብስብ ላይ የተናገሩት እጅግ ቁልፍ ሃሳብ ነበር። ይህም ሃሳብ “የዘውግ ፖለቲካ (የብሄር ፖለቲካ) ባለባቸው ሃገራት ሊበራል ዲሞክራሲ ብቻውን በቂ ምላሽ አይሰጥም ከዛ በተጨማሪ ውክልናን የሚያረጋግጥ ሂደት ያሸዋል” በሚል ያስቀመጡት አንኳር ነጥብ ነበር። አዘጋጆች ይህን ቁልፍ ንግግር እንዴት እንደዘነጉት አላውቅም። ይህ መሰረታዊ መርሆ በየትኛውም መልኩ ሊጣስ ሲታሰብ የሚያስከትለው አፀፋዊ ምላሽ መኖሩ እምብዛም አይገርምም።
እዚህ ጋር የእምነት ተዋፅኦን ከግምት ያስገባ ይሁን ሲባል እና የእምነት ተቋማት በስብስቡ ይገኙበት ማለት ሁለቱ እጅግ የተራራቁ ጉዳዮች ናቸው። የእምነት ተቋማት እንደ ማንኛውም የሙያ ይሁን ሌሎች የማህበራት ስብስብ የተወሰነ ድርሻ ሊኖራቸው ይችል ይሆናል። ነገር ግን ሃገር አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ የሚመክሩ የፖለቲካ መድረኮች እና ጉባኤዎች ግን የሁሉንም ውክልና ያንፀባረቁ ሊሆኑ ይገባል ሲባል ግን የተለየ ነው። ለምሳሌ የቪዥን ኢትዮጵያ ስብስብ መድረኩ የብሄር ስብስብ ጉዳይ ሚወራበት ስለሆነ አይደለም የብሄር ተዋፅኦው ይጠበቅ ሚባለው። እንደዛች ሃገር አንድ የማህበረሰብ ክፍል የዛን ብሄር ፍላጎት ፣ ስሜት ፣ እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን የሚመለከቱ በግንባር ቀደምትነት እነሱ ስለሆኑ ነው። የዛን ማህበረሰብ ፍላጎት እና ጥቅም የሚያስጠብቁት ነገሮችን በቅርበት በመሳተፍ እና በቅርበት ጉዳዩን በማየት ነው ። የእምነት ተዋፆኦንም ከግምት ያስገባ በሚባልበት ግዜ እንደ ብሄሩ ሁላ የእምነቱንም ተከታዮች ፍላጎት እና ጥቅም ከግምት ያስገባ ስለሚሆን ነው።
ስለሆነም የፖለቲካ መድረኮቻችንን ከእምነት የሰበካ ቦታ በማፅዳት ሴኩላራዊ በማድረግ እና የጋራ እ ሴቶቻችንን በጋራ ፣ በእኩልነት እና በመተማመን በመገንባት የኔነት ስሜቱን ፈጥረን ወደ እውነተኛ አንድነት እና መቀራረብ እንጓዝ። የህዝቦችን ውክልና ማስተናነስ ወይም ቦታ ያለመስጠት ደግሞ ለዘለቄታዊ የፍትህ መጓደል አደጋ ይሆናል። ሰላም እና መረጋጋት ብሎም ለምንሳሳላት ሃገራችን ከቃላት በዘለለ እና በውስጣችን በሰረፀ እኩልነት ላይ ተመርኩዘን መጻኢት ኢትዮጵያን ዲሞክራስያዊ እና ፍትሃዊ ልናደርጋት ግድ ይለናል።