የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ከባለድርሻ አካላት ጋር ዓርብ ባካሄደው የምክክር መድረክ የግል አየር መንገዶች ተወካዮች የሚያንቀሳቅሷቸው አነስተኛ አውሮፕላኖች ከግዙፉ አውሮፕላኖች ጋር እየተጋፉ መሥራት እንደተቸገሩ ተናግረዋል፡፡
የአቢሲኒያ የበረራ አገልግሎት ምክትል ማኔጂንግ ዳይሬክተር ካፒቴን አማረ ገብረሃና እንደገለጹት፣ የአዲስ አበባ ኤርፖርት አንድ መንደርደሪያ ያለው ሲሆን የአውሮፕላን እንቅስቃሴ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል፡፡ ‹‹እንደ ቦይንግ 777 እና 787 ያሉ ግዙፍ አውሮፕላኖች የሚጠቀሙበት ኤርፖርት ነው፡፡ እኛ ደግሞ እንደ ሴስና ያሉ አነስተኛ አውሮፕላኖችን ነው የምናንቀሳቅሰው፡፡ ትላልቅ አውሮፕላኖች ሊነሱ ወይም ሊያርፉ ሲሉ ጠብቁ እንባላለን፡፡ በእርግጥም ቅድሚያ መሰጠት ያለበት ለትላልቅ አውሮፕላኖች ነው፡፡ ነገር ግን እኛ በዕቅዳችን መሠረት መሥራትና መብረር አልቻልንም፡፡ ‹‹የአብራሪዎች ትምህርት ቤት ከፍተን በማስተማር ላይ ነን፡፡ 13 ያህል አነስተኛ አውሮፕላኖች አሉን፡፡ ተማሪዎቻችንን በበቂ ሁኔታ በረራ መለማመድ አልቻሉም፤›› ብለዋል፡፡
ካፒቴን አማረ ወደ ክልል ሄደው እንዳይሠሩ ገበያው ያለው አዲስ አበባ መሆኑን ጠቅሰው፣ የአነስተኛ አውሮፕላኖች እንቅስቃሴ እየጨመረ በመምጣቱ አነስተኛ አውሮፕላኖች የሚገለገሉበት አማራጭ ኤርፖርት መሥራት አስፈላጊ መሆኑን በአንክሮ ተናግረዋል፡፡ ሌሎችም የግል አየር መንገዶች ድጋፋቸውን ገልጸዋል፡፡
ከበረራ ፈቃድ ጋር በተያያዘ ለመከላከያ ሚኒስቴር ከ24 ሰዓት በፊት አሳውቁ የሚለው መመርያ አስቸጋሪ እንደሆነባቸውም የግል አየር መንገዶች ተናግረዋል፡፡ ደንበኞች አስቸኳይ የበረራ አገልግሎት እንደሚፈልጉ፣ አንዳንዴም የአየር አምቡላንስ አገልግሎት እንደሚጠየቅ ይህም ለሥራቸው እንቅፋት እንደሆነባቸው የግል አየር መንገድ ተወካዮች ተናግረዋል፡፡ ካፒቴን አማረ በተለይ ወደ ሰሜን ኢትዮጵያ በረራ ማድረግ አስቸጋሪ እንደሆነና ሠራተኞቻቸውም የታሠሩበት አጋጣሚ እንዳለ ጠቁመዋል፡፡
መንግሥት በማዘጋጀት ላይ ያለው አዲስ የአየር ትራንስፖርት ፖሊሲ የት እንደደረሰ የስብሰባው ተሳታፊዎች ጠይቀዋል፡፡
ሌላው ጠንከር ያለ ጥያቄ የተነሳው የአውሮፕላን መቀመጫ ጥያቄ ነው፡፡ የናሽናል ኤርዌይስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ካፒቴን አበራ ለሚ የግል አየር መንገዶች ላይ የተጣለው የአውሮፕላን መቀመጫ ገደብ የግል አየር መንገዶች እንዳያድጉ ተፅዕኖ እንዳደረገ ተናግረዋል፡፡
ቀደም ሲል የነበረው መመርያ የግል አየር መንገዶች ከ20 መቀመጫ በላይ ላይ ያለው አውሮፕላን እንዳይጠቀሙ ይከለክል ነበር፡፡ በቅርቡ ይህ መመርያ ተሻሽሎ ገደቡ ወደ 50 መቀመጫ ከፍ ተደርጓል፡፡ የግል አየር መንገድ ባለቤቶች በማሻሻያው ብዙም የተደሰቱ አይመስልም፡፡
ካፒቴን አበራ እንደሚሉት በአሁኑ ወቅት አምራቾች 50 መቀመጫ ያለው አውሮፕላን አያመርቱም፡፡ ‹‹በፊት 50 መቀመጫ ያለው አውሮፕላን የሚያመርተው ኩባንያ ፎከር ነበር፡፡ እሱም ከስሮ ተዘግቷል፡፡ ከራሺያ ያረጁ አውሮፕላኖችን እንዳናመጣ 22 ዓመት በላይ ዕድሜ ያለው አውሮፕላን እንዳናስገባ የሲቪል አቪዬሽን መመርያ ይከለክለናል፡፡ አነስተኛ መቀመጫ ባለው አውሮፕላን ተሠርቶ ትርፋማ መሆን አይቻልም፡፡ አቅም ካለኝ ቦይንግ 737 አውሮፕላን አምጥቼ እንድሠራ ለምን አይፈቀድልኝም?›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
ለጥያቄዎቹ ምላሽ የሰጡት የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ኮሎኔል ወሰንየለህ ሁነኛው፣ የአማራጭ ኤርፖርት ጥያቄን በተመለከተ ያለው ፍላጐት አስገዳጅ እየሆነ እንደሚመጣ ተናግረዋል፡፡ ትላልቅና አነስተኛ አውሮፕላኖችን በአንድ ኤርፖርት ማስተናገድ አስቸጋሪ መሆኑን ኮሎኔል ወሰንየለህ አምነው የተቀበሉት ጉዳይ ነበር፡፡
‹‹ጥያቄው ተገቢ ነው፡፡ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ በአዲስ አበባ ኤርፖርት ትላልቅና ትናንሽ አውሮፕላኖችን ማስተናገድ የማይቻልበት ሁኔታ ላይ ይደረሳል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ ሥልጠናውን ወደ ድሬዳዋ ለመውሰድ ተገዷል፤›› ያሉት ኮሎኔል ወሰንየለህ፣ በክልል ከተሞች ብዙ ሚሊዮን ብር ፈሶባቸው የተገነቡ አንዳንድ ኤርፖርቶች ብዙም አገልግሎት እንደማይሰጡ ጠቅሰዋል፡፡ የግል አየር መንገዶች እነዚህን ኤርፖርቶች ይጠቀሙ ወይስ በአዲስ አበባ ሁለተኛ ኤርፖርት ይገንባ የሚለው የመንግሥትን ውሳኔ የሚሻ ጉዳይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽንና ጉዳዩ በዋነኛነት የሚመለከተው የኢትዮጵያ ኤርፖርቶች ድርጅት ከትራንስፖርት ሚኒስቴር ጋር መክረው በበላይ አካል የሚወሰን ጉዳይ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡
ከመከላከያ ጋር ተያይዞ የተነሳውን ጥያቄ አስመልክቶ ዋና ዳይሬክተሩ በሰጡት ምላሽ መከላከያ፣ የአገር ደኅንነት የማስጠበቅ ኃላፊነት ያለበት ተቋም መሆኑን፣ የደኅንነት ሥጋቶች መኖራቸውን፣ ባለሥልጣኑ የበረራ ፈቃዶችን በተመለከተ ከመከላከያና ከመረጃና ደኅንነት መሥሪያ ቤቶች ጋር ተባብሮ እንደሚሠራ አስረድተዋል፡፡
የአገር ደኅንነት የማስጠበቅና አየር መንገዶችን ፍላጐት በሚያስታርቅ መልኩ ወጥ የሆነ አሠራር ለመቅረፅ ከመከላከያ ሚኒስቴር ጋር እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ‹‹በጋራ ያዘጋጀነው ሰነድ አለ፡፡ ያልተመለሱ ጥያቄዎች ስለነበሩ ጊዜ ወስዶብናል፡፡ በቅርቡ ተጠናቆ ግንዛቤ ማስጨበጫ ውይይት በቅርቡ እናዘጋጃለን፤›› ብለዋል፡፡
የአውሮፕላን ዕድሜ ገደብን በተመለከተ ማብራሪያ የሰጡት የአገር በረራ ደኅንነት ፕሮግራም (State Safety Program) ኃላፊ ሻምበል ግርማ ገብሬ፣ አፍሪካ የአሮጌ አውሮፕላኖች መጣያ መሆኗን በዚህም የአፍሪካ የበረራ ደኅንነት አስከፊ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
‹‹ባለን መረጃ መሠረት ብዙ ጊዜ የሚከሰቱ አደጋዎች በአሮጌ አውሮፕላኖች የሚከሰቱ ናቸው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ሩሲያ ሠራሽ አሮጌ አውሮፕላኖች አምስት ጊዜ ያህል ተከስክሰዋል፡፡ በናይጄሪያ በተደጋጋሚ የተከሰከሱት አሮጌ ቦይንግ 727 አውሮፕላኖች ናቸው፤›› ብለዋል፡፡
የአውሮፕላን ምዝገባና ፈቃድ ክፍል ተወካይ አቶ ዘውዱ ተክላይ በበኩላቸው 22 ዓመት የሚለው ገደብ እንዲያው ዝም ብሎ የተጣለ ሳይሆን ከዓለም አቀፉ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት ምክረ ሐሳብ የተወሰደ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
የግል አየር መንገዶች የግራውንድ ሃንድሊንግና ፋስሊቴሽን ሥራዎች ለግል ኩባንያዎች እንዲፈቀድ የጠየቁ ሲሆን፣ እነዚህና ሌሎች ጥያቄዎች በአዲሱ የአየር ትራንስፖርት ፖሊሲ ምላሽ እንደሚያገኙ ኮሎኔል ወሰንየለህ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡
ዓለም አቀፉ የሲቪል አቪዬሽን ድርጅት የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ድርጅትን በመጪው ሚያዚያ ወር እንደሚመረምረው ከመድረኩ ተነግሯል፡፡ ለዚህም ባለሥልጣኑ ሰፊ ዝግጅት በማድረግ ላይ መሆኑን አየር መንገዶች ከባለሥልጣኑ ጋር ተባብረው እንዲሠሩ ጥሪ ቀርቧል፡፡
ባለሥልጣኑ በየጊዜው ዘመናዊ የበረራ መቆጣጠሪያ መሣሪያዎች በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ በመግዛት በመትከል ላይ ሲሆን፣ በርካታ የአቪዬሽን ባለሙያዎችን በመቅጠርና በማሠልጠን ላይ ይገኛል፡፡ በ2007 በጀት ዓመትም 102 ሚሊዮን ብር ካፒታል በጀት በመመደብ የተለያዩ መሣሪያዎች ግዥና ተከላ ሥራ እንደሚያካሂድ ለማወቅ ተችሏል፡፡
በአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ለተተከለው ዘመናዊ ራዳር መጠባበቂያ የሚሆን መሣሪያ 30 ሚሊዮን ብር፣ ለኮሙዩኒኬሽን መሣሪያዎች ግዥ 25 ሚሊዮን ብር በጀት መበጀቱን ለማወቅ ተችሏል፡፡
በተያያዘ ዜና ሪፖርት ለማያቀርቡ የግል አየር መንገዶች የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ማስጠንቀቂያ ሰጠ፡፡ የአየር ትራንስፖርትና ዕቅድ ዳይሬክተር አቶ እንደሻው ይገዙ ከ2006 ዓ.ም. ጀምሮ የኢንቨስትመንት ፈቃድ የወሰዱ የግል አየር መንገዶች ስለ ሥራቸው እንቅስቃሴ በየሦስት ወራት ለባለሥልጣኑ ሪፖርት ማድረግ የሚጠበቅባቸው ቢሆንም፣ ግዴታቸውን እየተወጡ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ሪፖርት አለማቅረብ ፈቃድ የመሰረዝ ዕርምጃ ሊያስወስድ ይችላል፡፡ ስለዚህ ይህ ማሳሰቢያ ተወስዶ ግዴታችሁን እንድትወጡ እናሳስባለን፤›› ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ 15 የተመዘገቡ የግል አየር መንገዶች ያሉ ሲሆን፣ ወደ ሥራ የገቡት 10 ያህሉ ብቻ ናቸው፡፡ አየር መንገዶቹ የሚሰጡት የቻርተር በረራ አገልግሎት ሲሆን፣ የሚድሮኩ ትራንስኔሽን ኤርዌይስ ከጥቅምት 22 ጀምሮ መደበኛ የአገር ውስጥ በረራ በመስጠት ብቸኛ የግል አየር መንገድ ለመሆን ችሏል፡፡