እኔ የምለው ጥቁር ጣልያን ነው እንዴ የሚገዛን?
መቼም በዚህች ምርድ ላይ ሃብታም ሆኖ መኖር የማይፈልግ የለም። በሃብት ቁንጮ ላይ ለመቀመጥ የማይጥር የለም። ታዲያ የሮጠ ሁሉ አንደኛ እንደማይወጣ ሁሉ ቢሊዮነር ሆነው የሚታዩት ጥቂቶች ናቸው። እነዚህ የአለማችን ቢሊዮነሮች በተሰማሩበት የስራ ዘርፍ ላይ ቅድሚያ እንዲጠቀም ወይም መጥቀም የሚፈልጉት የራሳቸውን ዜጋ ነው። የአገራቸው ዜጋ ፍላጎቱ ከተሟላ ወይም ከበቂ በላይ የሚሆን ምርት ካመረቱ ወደ ሌላ አገር መሸጥም ሆነ መርዳት ይጀምራሉ። ይህ በአብዛኛው አገራት የሚሰራበት አሰራር ነው። አንድ ባለሃብት የሚያመርተው ምርቱን ቅድሚያ ለአገሩ ማዋል ግዴታ አለበት ለህዝቡም በቂ ምርት ማቅረብ ከተቻለ እና ትርፍ ሆኖ ከተገኘ ወደ ውጪ መላክ አንድ አገሩን እና ህዝቡን ከሚወድ ዜጋ የሚጠበቅ ነው። ታዲያ የኛ ሃብታሞች ምን ነካቸው?
ኢትዮጵያ ውስጥ የኑሮ ውድነትን የፈጠሩት መንግስት ያደራጃቸው የምንግስት ባለስልጣናት አብሮአቸው ከሚሰራው ልማታዊ ባለሃብቶች ለህዝባችን ማሰብ ባለመቻላቸው ከፍተኛ የሆነ እራስ ወዳድነት እና እራስን ለጥቅም አሳልፈው የሰጡ በመሆናቸው ነው።
የኢትዮጵያ ባላሃብቶች ከጥቂቱ በስተቀር ወደ ቢዝነስ ውስጥ ሲገቡ ህዝብን ለመጥቀም የህዝብን ኑሮ ለማሻሻል ሳይሆን በቀላሉ ትርፋማ ሆኖ ሚሊዮነር መሆን የሚችሉበትን መንገድ በቀላሉ ገንዘብ ማግኘት ወደሚችሉበት ያቶኩራሉ።
ባላሃብቶቹ ወደ ቢዝነሱ ከመግባታቸው በፊት እያንዳንዱ ባለሃብት ከአንድ ባለስልጣን ጋር መጣበቅ ግድ ይላቸዋል ካለበለዛ ግን ማነቆዎቹ ብዙ ስለሚሆኑ አገር ጥሎ መውጣት ካልሆነ በቀር በአገሩ ውስጥ በነጻነት የመስራት መብት አያገኝም። የዱባዬ አገር ህግ አንድ የውጪ ዜግነት ያለው ባለሃብት የቢዝነስ ተቋም በዱባዬ ለመስራት ቢፈልግ ከአንድ ዱባዬ ዘግነት ካለው ሰው ጋር መሆን አለበት ካለበለዛ ግን ምንም አይነት ስራን ማከናወን አይቻልም። ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ዜጋችን እንደ ውጪ ዜጋ ተቆጥሮ ስልጣን ላይ ካሉት አካል ጋር ተጣብቀህ አብሮ ካልሆነ በስተቀር ልማታዊ ባለሃብት መሆን አይቻልም። ታዲያ ኢትዮጵያ ማለት የነእንትና ቡድን ናት ማለት ነው እንዴ? በአንድ ወቅት የጣልያን ማፍያ ቡድን በጣም ተጠናክረው ጣልያን ውስጥ ያለውን ትላልቅ ቢዝነሶችን በሙሉ በነሱ ስር ካልሆነ በስተቀር መንቀሳቀስ ወደማይቻልበት ደረጃ አድርሰውት ነበረ በኋላ ግን የጣልያን መንግስት ጠንካራ እርምጃ በመውሰድ ነገሮችን ሊያስተካክል አድርጓል። ዛሬም ኢትዮጵያ ውስጥ እየሆነ ያለው ይሄ ነው። የኛዎቹ ከጣልያን ማፊያ የሚለዩት በመንግስት ደረጃ የተደራ ዘራፊዎች መሆናቸው ነው።
ህዝብን የሚጎዳ ባለሃብትም ይሁን ህዝብን የሚጨቁን መንግስት በኢትዮጵያ ይኖር ዘንድ አይገባም። ባለሃብቱም መንግስትም ዘላለማዊ በሚመስልቸው ጥቅም ውስጥ የተቀመጡ ቢመስላቸውም ቅሉ ሃብትም ይጠፋል ስልጣንም ይሻራል ህዝብ ግን ሁል ግዜ ኗሪ ነው። ህዝብን እያስራቡ ሃብታም ለመሆን ከመጣር ህዝብን እየረገጡ ስልጣን ላይ ለመቆየት ከማሰብ ትቆጠቡ ዘንድ ግድ ይላችኋል። ነገሮች እንዳሉበት ይቀጥላል ብሎ ማሰብ ሞኝነት ነው። ሁኔታዎች ሲቀየሩ የናንተም እጣ ፈንታ አደጋ ውስጥ ነውና ከወዲሁ ስለ አገር ክብር እና ስለ ህዝብ ፍቅር አርቆ ማሰብ ብልህነት ነው።
በኢትዮጵያ ውስጥ ህዝባችንን በማስራብ በቀላሉ መመገብ የሚችላቸውን ምግቦች በማስወደድ የውጪ ዜጋን በመመገብ ስራ ላይ የተሰማራቹ ልማታዊ ባለሃብቶች ለህዝባችን በማንኪያ ህዝባችን ላልሆኑት ደግሞ በጭልፋ በማቀበል ዶላር ቆጠራ ይቁም።
የእንስሳት ስጋን ወደ ውጪ በመላክ የተሰማራችሁ ፣ በጥራ ጥሬ እህሎች ላይ፣ የቅባት እህሎች ላይ፣ ፍራፍሬ ምርቶች ላይ፣ የቅባት እህሎች ላይ የተሰማራችሁ ባለሃብቶች ህዝባችን ላይ በእለት ከእለት በሚመገባቸው ምግቦች ላይ የዋጋ ውድነትን በማምጣት ኑሮውን ያከበዳችሁት እናተው ስለሆናችሁ በእንደነዚ አይነት ስራ ለይ የተሰማራችሁ ሰዎች መጀመሪያ ህዝባችንን መመገብ ከዛም ለህብረተሰባችን በቂ ምርቶችን ማቅረብ ቀጥሎም የሚያስፈልጉትን ነገሮች ቅድሚያ ለአገርሬ ሰው ማቅረብ ይገባችኋል እንጂ በበቂ ሁኔታ ህዝባችን ሳይዳረሰው ወገባችሁን ታጥቃችሁ ውጪአዊያኖችን ለመመገብ ስራ ላይ የተሰማራችሁ ባለሃብቶች ከዚህ ድርጊታችሁ ተቆጥባችሁ ቅድሚያ ወገንን ወደመመገቡ ስራ በመግባት የስራ ዘርፋችሁን ትቀይሩ ዘንድ ግድ ይላችኋል።
የስጋ ተዋጽኦ ወደ ውጪ ከመላኩ በፊት የአንድ ኪሎ ስጋ በኔ ከስምንት አመት በፊት 20 ብር ነበረ አሁን ግን የሙክት በግ ዋጋ ደርሷል። አንድ በግ ከፍተኛው ዋጋ 500 ብር ሲሆን አሁን ግን 5000 ደርሷል። አንድ በሬ በፊት ከፍተኛው 5000 ሲሆን አሁን ግን 40.000 ደርሷል። ይህም የሆነበት ምክንያት የስጋ ምርቶች በከፍተኛ ሁኔታ ወደ ውጪ በመላክ በህዝባችን ላይ ለፈጠረውን የዋጋ ውድነት እና የኑሮ ቀውስ ተጠያቂ ያደርጋችኋል።ስጋ ላኪ ድርጅቶች የሚገበያዩት በዶላር ስለሆነ የዋጋ መናርን ቢያመጡም መንግስት ምንም አይጠይቃቸውም ምክንያቱም መንግስት ዶላሩ ይምጣለት እንጂ ህዝባችን ስጋ ቢበላም ባይበላም ቢወደድበትም ባይወደድበትም ግድ የለውም። ከመንግስት አካሎች ጋር በመጣበቅ እራሳችሁን ሚሊዮነር በማድረግ ስራ ላይ የተሰማራችሁ ልማታዊ ባለሃብቶች ህዝባችን ከሚጎዳ ስራ ትታቀቡ ዘንድ ግድ ይላችኋል።
በጥራጥሬም ዘርፍ የተሰማሩ እንደዚሁ ነው። የጥራጥሬን እህሎች በቀላሉ ከገበሬው በመግዛት በሰሩት ትላልቅ መጋዘን ውስጥ በማጠራቀም ለውጪ ሽያጭ ያውሉታል። በፊት አንድ ኪሎ ምስር 2 ብር ገዝቶ ይመገብ የነበረው ህዝባችን ዛሬ 60 ብር ሆኗል። ከውድነቱ የተነሳ ምስርን እንደ ስጋ ጣል ጣል አድርጎ የሚመገቡ የህብረተሰባችን ክፍሎች በጣም ብዙ ናቸው። በመንግስት ድጋፍ ጥቂት ሚሊዮነሮችን ለመፍጠር አገርን ማስራብ ገዚው መንግስት ለህዝብ ያለውን ጥላቻ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነውና ህዝቤ ሆይ በህዝብ ሃብት እና ንብረት የሚቀልዱትን አንባ ገነኖችን ሁሉ ለፍርድ ለማቅረብ በህብረት በመሆን ለነጻነትህ፣ ለክብርህ፣ ለህልውናህ፣ የምትታገልበት ግዜ ነውና ቆርጦ መነሻው ሰዓቱ አሁን ነው። ካለበለዛ 60 ብር የነበረው ምስር አይናችን እያየ በቅርቡ 100 ከዛም 200 ብር ይገባል። የህዝባችን ሃዘን ለገዚዎቻችን የደስታ ዜማ መሆኑን አትርሱ።
ከየአንዳንዱ ባለ ሃብት በስተጀርባ የባለስልጣናቱ ጥምረት እንዲኖር የተፈለገበት ዋናው አላማ በስልጣን ላይ ያሉት አካላት የኢትዮጵያን ሃብትና ንብረት በነሱ ስር ካልሆነ በስተቀር በየትኛውም የቢዝነስ ስራ ውስጥ መሳተፍም ሆነ መስራት አይችልም የሚል የጥቂቶች የማፍያ ድርጅት መመሪያ ስላለ ነው። በነጻነት ስም አገርን ለመዝረፍ ተደራጅቶ ጫካ መግባት ቢያሳፍርም ቅሉ የኋላ ኋላ የዘረፉትን የሃገር ሃብት ሳይበሏት ዋጋ የሚከፍሉበት እንደሆነ ብናውቅም ከነዚህ ጥቂት የአገር ንብረት ዘራፊ ጋር ተጣብቀው የህዝብን ኑሮ የሚያውኩ ባላሃብቶች የሚንቀሳቀሱት በህግ መሰረት ሳይሆን አብሮት ከተጣበቀው ባለስልጣን ህግ መሰረት ነው። በኢትዮጵያ በስራ ላይ የተሰማሩትን ባለ ሃብት የመቆጣጠሩ ስራ አብሮ ያለው ባለስልጣን ድርሻ ነው። የኢትዮጵያ ህግ እነሱን አይመለከታቸውም። ባለሃብቱ ከተሰመረላቸው መስመር ፈቀቅ ካሉ ሙስና የሚል ህግ ይመዘዝባቸውና ወደ እስር ይወረወራሉ ከመስመሩ ካልወጡ ግን የኢትዮጵያ ህግ በነሱ ላይ አይሰራም።
አንድ ስሙን መጥቀስ የማልፈልገው ባለሃብት ያመረታቸውን ምርቶች መኪናዎቹ ከሚችሉት አቅም በላይ ጭኖባቸው ሲሄድ ኬላ ላይ ይያዛል የኬላ ሰራተኞችም እንደዚህ ጭነህ ማለፍ አትችልም መኪናዎቹ ከሚችሉት አቅም በላይ ተጭኖባቸዋል ስለዚህ አደጋ ሊታደርስ ትችላለህና ህግም ተላልፈሃልና ትቀጣለህ በተጨማሪም ትርፍ የጫንካቸውን አውርደህ ነው ማለፍ የምትችለው ይሉታል። የዚህን ግዜ ባለሃብቱ በጣም በመናደድ እንዴት ደፈራችሁኝ አታውቁኝም እንዴ እያለ ከህግ በላይ መሆኑን ሊያሳያቸው ህግ እሱጋር እንደማይሰራ ሊነግራቸው ስልክ አውጥቶ ይደውልና ትንሽ ካወራ በኋላ ለኬላ ሰራተኛ አላፊ ስልኩን ይሰጠዋል የኬላ ሰራተኛውም ስልኩን ካናገረ በኋላ ስልኩን ለባለሃብቱ ይመልስለትና ሰላምታ በመስጠት ይቅርታ ጠይቆት ማለፍ እንደሚችል ይነግረዋል። ባለሃብት የደወለው አብሮት ከሚሰራው ባለስልጣን ጋር ነው። ለኬላው ሰራተኛ የተናገረው የማይመለከትህ ጉዳይ ላይ አትግባ ካለበለዛ ትወገዳለህ የሚል ነበረ። ከጥቂትም ሰዓት በኋላ መኪናውን የሚያጅቡ የታጠቁ ሲብል ለባሽ በላንድክሩዘር መኪና መጥተው አጅበውት ዬዱ። እየተሰራ ያለው እንደዚህ ነው ህግ አይሰራም በየመስራቤቱ ትክክለኛ ስራን የሚሰሩ ሰራጠኞችን ከበላይ ቀጭን ትዛዝ በመስጠት በአገሩ ለአገሩ በትክክለኛ መንገድ እንዳይሰራ እያሸማቀቁ ሌባና ቀማኛ የበዛባት አገር እንድትሆን እየሰሩ ያሉት ጥቂቶች ናቸው። ጥቂቶችን ለማኖር አገርም ሆነ ህዝብ ቢጠፋ ግዴ በሌላቸው ሰዎች ኢትዮጵያ እየመሯት እንዳለ የምናይበት ነው።
የውጭ መንግስታት ሆኑ ባለሃብቶች ከማንኛውም በፊት ቅድሚያ ለህዝባቸው ነው የሚሰጡት። የህዝባቸውን ፍላጎት ለማሟላት የአገራቸው ምርት አናሳ ሆኖ ካገኙት ከውጪ በመግዛት የህዝባቸውን ፍላጎት ሊያሟሉ ይጥራሉ። የኛዎቹ መንግስትና ባለሃብት ደግሞ የውጪ አገር ፍላጎትን ለማሟላት ህዝባችንን ያስርባሉ። ተገላቢጦሽ ማለት ይሄ ነው። እኔ የምለው ጥቁር ጣልያን ነው እንዴ የሚገዛን?።
የኛ ባለሃብቶች መጀመሪያ አእምሮአችሁን ቀይሩት ለወገንና ለአገር ማሰብ የሚችል አድርጉት ለጥቅማችሁ እና ጥቂቶችን በመታዘዝ መኖራችሁን አቁሙ ወደ ውጪ ከመላካችሁ በፊት ቅድሚያ ለህዝባችን በበቂ ሁኔታ የምግብ ፍላጎቶች ተሟልቷል ወይ ብላችሁ ፍላጎቶችን ለሟማሟላት ጣሩ የህዝብን መሰረታዊ የምግብ ፍላጎት ከተሟላ በኋላ ከህዝብ የተረፈው ወደ ውጪ በመላክ ስራ ውስጥ እንድትሰማሩ የንጹሃን አእምሮ ባለቤት፣ አገር የመውደድ ሃሳብ፣ ህዝብን የማፍቀር ልቦና፤ ሊኖራችሁ ግድ ይላል። የህዝብ መሰረታዊ የምግብ ፍላጎት ሳይሟላ ከህዝብ ጉሮሮ ላይ እየነጠቃችሁ ጥቂቶችን የማኖር ስራ እና የውጪ አገር ዜጋ የመመገቡ ሁኔታ በአፋጣኝ መቆም አለበት። በኢትዮጵያ ውስጥ በምግብ ውጤቶች ላይ ዋጋው እንዲንር በማድረግ እናንተ እና የናንተ አዛዦች ተጠቃሾችም ተጠያቂዎችም ናችሁ።
ከተማ ዋቅጅራ
29.09.2015
Email- waqjirak@yahoo.com