Quantcast
Channel: ዘ-ሐበሻ – Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 8745

Health: ወንዶች በፍፁም ችላ ሊሏቸው የማይገቡ 4 አደገኛ የጤና ችግር ምልክቶች

$
0
0

Health ethiopia
ጤናና ገንዘብ አያያዝን ጨምሮ በብዙ ነገሮች ጥንቃቄ በማድረግ ከወንዶች በተሻለ ሴቶች ፈጣን ናቸው፡፡ ጥናቶች እንደሚያሳዩት የሚበዙት ወንዶች ግን በተለይ የጤና ችግሩ የሆስፒታል አልጋ ላይ የሚጥል ካልሆነ በቀር በምልክቶች መነሻነት ወደ ሆስፒታል መሄድን ልምድ አላደረጉም፡፡ ነገር ግን ይህ የቸልተኝነት ልምድ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወንዶችን ከክፉ የጤና ችግር እስከሞት በሚያደርስ አደጋ ላይ እየዋለ መሆኑን ጥናቶች እያመለከቱ ነው፡፡

ችላ የማይገባቸው የጤና ችግሮች
የ52 ዓመቱ ሰው አቶ ግርማ ደጋግሞ ያስቸግራቸው የነበረውን ተደጋጋሚ የትንፋሽ ማጠር በምንም ምክንያት ከክፉ የጤና ችግር ጋር የተያያዘ ነው ብለው አስበው አያውቁም፡፡ አንድ ቀን ግን ነገሮች ተጣደፉና ሐኪም ቤትን በድንገተኛ ታካሚነት መጎብኘት ግዴታቸው ሆነ፡፡ ምርመራ ያደረገላቸው ሐኪም ችግሩ ከልባቸው ጋር የተያያዘ መሆኑንና ሳምባቸውም ውሃ ሳይቋጥር እንዳልቀረ ሲነግራቸው ከፍተኛ ድንጋጤም ውስጥ ገቡ፡፡ የልብ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ከፍተኛ ኦፕሬሽን ማድረግ ግዴታ ሆኖባቸው ነበር፡፡ በተደጋጋሚ ችላ ይሉት የነበረውን የትንፋሽ ማጠር ተጠራጥረው ቀድመው ወደ ሐኪም ቢሄዱ ከፍተኛ የቀዶ ጥገና ህክምና ውስጥ ከመግባት ይድኑ እንደነበርም አቶ ግርማ ይገልጣሉ፡፡ ጥሩ አጋጣሚ ሆኖ የቅርብ ሰዎችና ባለቤታቸው እቤት ባሉበት ወቅት ችግሩ መከሰቱ ፈጣን ህክምና ለማግኘት አስቻላቸው እንጂ የትንፋሽ ማጠሩ የትም ሊከሰት እና ህይወታቸውንም ሊያሳጣቸው ይችል እንደነበር ሐኪሙ እንደገለጠላቸው እና እድለኛ እንደነበሩም ያስታውሳሉ፡፡

ሁሉም ሰው ግን እን አቶ ግርማ ዕድለኛ ሊሆን አይችልም፡፡ የህመም ምልክቶችን ችላ በማለት ቆይተው በቂ ህክምናን አግኝተው ከከባድ በሽታዎች የሚያገግሙ ሰዎችም ብዙ አይደሉም፡፡ አንዳንዴ እጅግ ከዘገዩ የሚታወቁ ምልክቶችም በቀጥታ ለዘላቂ የአካል ጉዳት አለዚያም ሞት የሚያደርሱበት ዕድል ሰፊ ነው፡፡ ከሴቶች በበለጠ ወንዶች የበሽታ ምልክቶችን ችላ የማለት እና የህክምናን እርዳታ ለመጠየቅም እጅግ እንደሚዘገዩ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ እንዲያውም በቅርቡ የተሰራ ጥናት እንደሚያመለክተው በብዙ አገራት ከ38 በመቶ በላይ ወንዶች ሆስፒታሎችን የሚጎበኙት ህይወትን አደጋ ላይ የሚጥል ችግር ሲገጥማቸው ብቻ ነው፡፡ ለዚህም ይመስላል ተደጋጋሚ ጥናትን ያካሄዱ ባለሙያዎች እባካችሁ ወንዶች የከፋ የጤና ችግርን ጠቋሚ ለሚሆኑት ምልክቶች ትኩረት አድርጉ ሲሉ የሚያሳስቡት፡፡

4. ሽንት መሽናት መቸገር፣ ደም የቀለመ ሽንት
ሽንት ሰውነት ቆሻሻን አጣርቶ የሚያስወጣበት ፈሳሽ እንደመሆኑ ጤነኛ መጠን፣ ቀለም እና ድግግሞሽ የሰውነትን የማጣራት አቅም እንዲሁም ኩላሊትና መላውን የማጣሪያ ስርዓት ጤንነት ደረጃ ይገልጣል፡፡ በወንዶች ዘንድ ከሚታዩ የችግር ምልክቶች አንዱ ሽንት ለመሽናት መቸገር ነው፡፡ በተለይ ሲሸኑ ህመም የሚሰማዎት ከሆነ እና መሽናት እየፈለጉ ከመፀዳጃ ቤት ሲደርሱ ግን የሚታገሉ ከሆነ ጉዳዩ የፕሮስቴት እጢ ችግርን ይጠቁማልና ቶሎ የሐኪም እርዳታን ይጠይቁ ሲሉ ይመክራሉ፡፡ የፕሮስቴት እጢ የወንድ ዘርን እንደልብ ለመቀስቀስ የሚያስችለውን ፈሳሽ የሚያመርት ከሽንት ከረጢት በታች የሚገኝ በጣም አነስተኛ ዕጢ ነው፡፡ የዚህ እጢ ችግር በጊዜ ካልተቀረፈ ከፕሮስቴት ካንሰር እስከ ልጅ የመውለድ ብቃትን ማሳጣት የሚያደርስ ጥፋት ሊያደርስ ይችላል፡፡
ሽንት በተፈጥሮ ጤናማ ቀለሙ ቢጫ ነው፡፡ ከዚህ በመጠኑ የተለየ ሽንት ማየት ከተመገቡት ምግብ ጋር የሚያያዝ ሊሆን ይችላል፡፡ ከዚህ ባለፈ ሁኔታ ግን በተደጋጋሚ ደም ማየት ከበድ ያለ ችግርን ጠቋሚ ምልክት ነው፡፡ ይህ መሰሉ ችግር የፕሮስቴት እጢ ካንሰርን ከመጠቆም ባለፈ የሽንት ቧንቧ መስመር መቆጣት፣ ኢንፌክሽን፣ የኩላሊት ጠተር እንዲሁም ሌሎች የኩላሊት በሽታ አይነቶች እየተከሰቱ መሆናቸውን አመላካች በመሆኑ በፍፁም ችላ ሊሉት አይገባም ሲሉ ባለሙያዎች ይመክራሉ፡፡

4. የደረት ላይ ህመም
ድንገትደረትን ስቅዝ አድርጎ የሚይዝ ህመም በአንድ ወይም በሌላ ጊዜ ገጥምዎት ሊሆን ይችላል፡፡ ይህ መሰሉ ምልክት ደገምገም የሚያደርግ ከሆነ ግን ብዙ የሚናገረው የጤና ችግር ስላለ ፈጣን እርምጃ ሊወስዱና ሐኪም ጋር ሊቀርቡም ይገባል ባይ ናቸው ባለሙያዎቹ፡፡ የደረት ላይ ህመም የልብ ድካምን ጠቋሚ ከመሆኑ በተጨማሪ እንደ ኒሞኒያ፣ አስም እንዲሁም ሌሎች ከምግብ መፍጫ ስርዓት ችግሮች ጋር የተያያዘ እክል እየተፈጠረ መሆኑን አመላካች ነው እና ችግሩ ገፍቶ እስኪመጣ መጠበቅና እራሱ በራሱ እንደሚሄድ መገመት ችግርን መጥራት ነው፡፡

3. ተደጋጋሚ ድብርት
ሁላችንም የየራሳችን መጥፎ ቀናት አሉን፡፡ ሰው ማናገር የምንጠላበት፣ የምንወደው ነገር ሁሉ ትርጉም የሚያጣበት እና በአጠቃላይ ሁሉ ነገር የሚያስጠላን ጊዜ አለ፡፡ ነገር ግን ይህ አልፎ አልፎ የሚከሰት እና በዕለት ተዕለት የህይወት እንቅስቃሴያችን ከሚከሰቱ ደስታችንን ከሚያደምኑ ጉዳዮች ጋር የሚያያዝ እና ችግሮቹ መፍትሄ ሲያገኙ አብሮ የሚፈታ ሊሆን ይችላል፡፡ ከዚህ አልፎ መደበኛ የህይወት አካል መሆን ሲጀምር ግን ከጀርባው ሌላ ያልተፈታ ስነ ልቦናዊ ወይም ማህበራዊ ችግርን ጠቋሚ ሊሆን ይችላል፡፡
ሴቶች ከወንዶች በተሻለ ድብርትን ለይቶ የማወቅና ምክንያቱን የመፈለግ እንዲሁም ከጓደኛና ቤተሰብ ጋር በመወያየት የመፍታት ተፈጥሯዊ ልምዶች አሏቸው፡፡ ወንዶች በተቃራኒው መጠጥን ትርጉም የሌለው ወሲብን እና እንደ ጫት መቃም የመሰሉ አጉል ልምዶችን በመተግበር ወይም መጠልን በመምረጥ ድብርታቸውን ለማስታገስ ቀዳሚው የባለሙያዎች ምክር ሲሆን ተደጋጋሚ ድብርት ደግሞ ህይወትን እስከማጣት የሚያደርስ ጥፋት ውስጥ ሊከት ስለሚችል በቅድሚያ በቅርብ ላለ የቤተሰብ አባል ወይም ጓደኛ ችግሩን ማዋራት፣ በዚያ የሚቀል ካልሆነ በአፋጣኝ ወደ ባለሞያ መቅረብና ዘላቂ መፍትሄ ማበጀት ይገባል፡፡ ድብርት ችላ አይበሉ!

ካንሰር በሁለቱም ጾታዎች ተደጋግሞ የሚታይ ችግር ቢሆንም በወንዶች ዘንድ ካንሰር በምርመራ ሲታወቅ ብዙ ጊዜ ዘግይቶ እና ለህክምናም አስቸጋሪ በሚሆንበት ደረጃ ላይ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ በምክንያትነት ከሚነሱ ጉዳዮች ቀዳሚው ወንዶች ዘንድ የአካላቶቻቸውን የተለያዩ ለውጦች አለመከታተላቸውና ችግር ሲኖርም የህክምና እርዳታን አለመሻታቸው ነው ሲሉ ባለሙያዎቹ ያስረዳሉ፡፡

ሴቶች የጡት ካንሰርን ቀድመው እንዲያውቁ ጡቶቻቸውን በየጊዜው እራሳቸው በእጃቸው እንዲፈትሹ እና የተለየ እብጠት ከተሰማቸው ለባለሞያ እንዲያሳዩ ይመከራል፡፡ በዚህም ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ሴቶች ካንሰርን በጊዜ መፍትሄ አብጅተውለታል፡፡ በወንዶች ዘንድ ከሚታዩ የካንሰር አይነቶች አንዱ የወንድ ዘር ፍሬ ማምረቻ (ቆለጥ) ውስጥ የሚከሰት ካንሰር ነው፡፡ ይህን የካንሰር አይነት እንደ ሴቶች ጡት ሁሉ ቀላል ፍተሻን ራሳቸው ወንዶች በቆለጦቻቸው ላይ በማድረግ ቀድመው ሊደርሱበትና በባለሞያም እርዳታ ሊያገኙበት ይችላሉ፡፡ ወንዶች ሰውነታቸውን በሚታጠቡበት ወቅት አጠቃላይ ሰውነታቸውን ማስተዋል፣ አልፎ አልፎም በቆለጥ አካባቢ የተፈጠሩ በደንብ የማያስታውቁ አነስተኛ እብጠት መሰል ነገሮች ካሉምመፈተሽ፣ ካንሰሩን ቀድሞ ለመለየት ይጠቅማልና ይህንን ችላ አይበሉ ሲሉ ባለሞያዎቹ ያስረዳሉ፡፡

2.የሆድ ድርቀት
ከምንመገባቸው ጋር በተያያዘ የሚፈጠር የሆድ ድርቀት ጊዜያዊ ችግር በመሆኑ ለወንዶች ብቻ ሳይሆን ሴቶችንም ይህን ያህል ስጋት ላይ የሚጥል ችግር አይደለም፡፡ ነገር ግን በተደጋጋሚ የሆድ ድርቀት ሲከሰት በተለይ ወንዶች ትኩረት መስጠት እና ዋናውን ምክንያት ለይቶ መፍትሄ ማበጀት የግድ ይሆንባቸዋል፡፡ የሆድ ድርቀት መሰረታዊ ምክንያቶች በርካታ ሊሆኑ ቢችሉም የአንጀት ካንሰርን መጠርጠር የብዙ ባለሞያዎች ቀዳሚ ግምት ነው፡፡ የሆድ ድርቀት ከጀርባው ካለው ምክንያት በተጨማሪም በራሱ ሌላ ጣጣንም ይዞ ይመጣል፡፡

የሆ ድርቀት በቀላል መወሰድ የሌለበት ዋና ምክንያት ሄሞሮይድ የተሰኘውና በተለምዶ የፊንጢጣ ኪንታሮት ብለን የምንጠራው በአብዛኛው ወንዶችን የሚያሰቃየውን ህመም ለመከላከል ነው፡፡ ሄሞሮይድ ይህ ነው የተባለ መነሻ ምክንያት ባይቀመጥለትም በሆድ ድርቀት ወቅት አይነምድርን ለማስወጣት በከባድ ማማጥ የግድ ይሆናል፡፡ በዚህ ጊዜም የፊንጢጣ አካባቢ ስለ ህዋሳት የመጎዳትና የመድማት አደጋ ይገጥማቸዋል፡፡ ይህ የህዋሳቱ ነርቮቹ መቆጣተ የፊንጢጣ ጫፍ እንዲገለበጥና መቀመጥና መቆም እንዲሁም አይነምድር መውጣት ትልቅ ፈተና እንዲሆን ያስገድዳል፡፡ ለህክምና አስቸጋሪ ከመሆኑ አንፃር አንዳንድ ሰዎች እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ በባህል ህክምና ችግሩን ሳያዳግሙ ለመንቀል ሲጥሩ ለተወሳሰበ ቀውስ የተዳረጉበትን ጊዜ የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ በቅርብ ያውቃል፡፡ የሄሞሮይድ ህመም እጅግ ከባድና ለማንም አይስጥ የሚባል አይነት ነው፡፡ ለዚህ ነው ረጅም ጊዜ የሚቆይ የሆድ ድርቀትን በባለሞያ እርዳታ በፍጥነት ማስወገድ የሚመከረው፡፡

1. የወሲብ ችግር
ሁሉም በሚቻል ደረጃ ወንዶች በአንድ ወይም በሌላ ጊዜ ብልታቸውን ለወሲብ ማቆም እና ከዚያም እስከወሲቡ ፍፃሜ የመዝለቅ ችግር ይገጥማቸዋል፡፡ 70 በመቶው የሚደርስ ለወሲብ ዝግጁ አለመሆን ችግር ከስነ ልቦናዊ ጉዳዮች ጋር የሚያያዝ በመሆኑ ጠለቅ ያለ ዳሰሳን ይጠይቃል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ግን የወሲብ ብልት አለመቆም ከበድ ካሉት የልብ ህመም፣ የስኳር ህመም እንዲሁም የደም ቧንቧ ችግሮች ጋር የሚያያዝ በመሆኑ በቀላል መውሰድ እንደማይገባ ባለሞያዎች ያሳስባሉ፡፡
በተፈጥሮ የወንድ ብልት ለወሲብ የሚቆመው ከአዕምሮ በሚሰጥ ትዕዛዝ ይሁን እንጂ ከልብ ተነስተው ወደ ብልት የሚነሳ የደም ቧንቧዎች ከልብ በሚወስዱት ደም ሲሞላ ነው ብልት የሚቆመው፡፡ በመሆኑም ማናቸውም በልብ እና ደም ቧንቧ ህመሞች ላይ የሚከሰት እክል በወሲብ ላይ እክል ያመጣል፡፡ የወሲብ ችግር ከአንድ ሰሞን አልፎ ተደጋጋሚ የሚሆንባቸው እና ብልታቸውን ማስነሳት የሚቸገሩ ሰዎች ችግራቸው ወሲብ ላይ ብቻ ሳይሆን ሰፋ ካሉት ሌሎች አካላትም ጋር ስለሆነ ይህንን ማስጠንቀቂያ የምር ወስደው አስቸኳይ የባለሙያ እርዳታ ማግኘት አለባቸው፡፡

በመነሻችን ታሪካቸውን ያካፈልናችሁ አቶ ግርማ ህይወታቸውን አደጋ ላይ የጣለውን ምልክት ሰዎች ችላ እንዳይሉ ደጋግመው ለወዳጆቻቸው ይነግራሉ፡፡ የትንፋሽ ማጠር ብቻ ሳይሆን ቀደም ብለን ያነሳሳናቸውም ምልክቶች ከበስተጀርባቸው ብዙ የጤና ችግሮቹን ይዘዋልና ትኩረትን ይሻሉ፡፡


Viewing all articles
Browse latest Browse all 8745

Trending Articles