Quantcast
Channel: ዘ-ሐበሻ – Ethiopian News | ዘ-ሐበሻ | Latest News Provider | News For All
Viewing all articles
Browse latest Browse all 8745

የአሁኑ የኢትዮጵያ ወጣቶች ትግል

$
0
0

ከአቻምየለህ ታምሩ

የኛ ብቻ ሳይሆን የመላው ዓለም ሕልም የሆነ ታላቅ ግብ አለ። ይህም ግብ ምድራዊ ገነትን ፈጥሮ የሰው ልጆች ከችግር፣ ከበሽታና ከድንቁርና ነጻ ወጥተው፤ ወንጀል፣ እስራት፣ ጭቆና፣ ግፍና የኑሮ ጭንቀት ተረስተው የሰው ልጆች በፍቅርና በደስታ እንዲኖሩ ለማድረግ መጣጣር ነው። ብዙ ሀገሮችም ከዚያ ገነት በመጠኑ ቀረብ ብለው አሁንም እርምጃቸውን እያፋጠኑ ወደዚያው ጨርሶ ለመግባት በመገስገስ ላይ ናቸው። በወያኔዋ ኢትዮጵያ የምንኖር እኛ ገባሮች ግን ከሁሉ በተለየ ሁናቴ ተፈርዶብን ከትግራይ በበቀለው አጥፊያችን የወያኔ ዘረኛ ቡድን ምክንያት ከገነቱ ቀርቶ ከመካነ-ንስሐው ሳንደርስ ገና በሲኦል ውስጥ ሁነን ስንሠቃይ እንገኛለን።

Tensaye

በሥልጣኔ ወደፊት ከገፉት አገሮች ጥቂቶችንም ሆነ ብዙዎችን የምዕራቦችንም ሆነ የምስራቆችን ያየ አንድ ያገሬ ልጅ የኢትዮጵያ ህዝብ እንደ ሰው ነው የሚኖረው ብሎ ማመን እጅግ ያስቸግረዋል። እኛ ኢትዮጵያን የምንኖረው ወያኔ ባበጀልን በቁም መቃብራችን ውስጥ ነው። ይህም የሆነው አባቶቻችን የሰሯትን አገር ልጆቻቸው ተረክበው እንዳባቶቻችን ወደፊት በማየት ለመጪው ትውልድ የሚሆን አገር መፍጠር ባለመቻላቸው ነው። ወደድንም ጠላንም ዛሬ ያለችው ልዩነትና ጥላቻን መሰረት ያደረገ የክልልና የፖለቲካ አገዛዝ የተንሰራፋባት፤ የጎሳ ድንበሮችን በማጠናከር የተወናከረ መንግስታዊ ስርዓት ላይ የተፈጠረችዋ «አዲሲቷ» ኢትዮጵያ በዚህ መልኩ እንዳለች ከቀጠለች ከመቶ አመት በኋላ ዛሬ የተፈጠሩት ተፎካካሪ ብሔረሰቦች [Rival Ethnic Nationalities] ርስ በራስ እየተከሳከሱ ሞትን ያነግሱና እያንዳንዳችን ከምድረ ገጽ ጠፍተን፤ «በኢትዮጵያ» ውስጥ የሚገኘው የኢትዮጵያ ህዝብ ሳይሆን የኢትዮጵያ ህዝብ መቃብር ብቻ ይሆናል። ስለሆነም ዛሬ የኛ የኢትዮጵያ ወጣቶች የመጀመሪያው ተግባራችን መሆን ያለበት ከምንኖርበት የቁም መቃብራችን መግነዛችንን ቀዳደንና በጣጥሰን የተጫነብንን የመቃብር ድንጋይና አፈር ፈነቃቅለን ወደ ብርሀን ዓለም የምንወጣበትን ከጥላቻ የጸዳችን የራሳችንን አገር መፍጠር ይሆናል። ይህንን ከግብ ለማድረስ በቅድሚያ የምንፈጥረው ዋናው ኃይላችን «በመወያት የተሠወረው ይገለጣል፤ የጠመመው ይቀናል እንዲሉ አበው» እኛ የዚህ ዘመን ኢትዮጵያውያን ወጣቶች በቅዱስ መንፈስ ተነሳስተን፤ ፍርሀትና አለመተማመንን አስወግደን በጋራ ችግሮቻቸው ዙሪያ እንደ አዲስ በፌስቡክና በትዊተር ዛሬዉኑ የምንቀሰቅሰው ውይይት ነው። ይሄ የምንጀምረው ውይይት የተባበረ ክንድና የጋራ ኃይል ለመፍጠር መሰረት የምንጥልበት የተባበረ ኃይላችን ነው።

ከዚያም በተባበረ ኃይላችን የራሳችንን አገር ገነት ለማድረግ ትግላችንን አጠናክረን እንቀጥላለን። በቆራጥነትም እንራመዳለን። በምንፈጥረው ገነት እኛ አሁን ያለነው ሰዎች ገብተን ልንንቧች መጓጓት የለብንም። ለዚህ ብንታደል ኖሮ አባቶቻችን እኛ እያጋጠመን ያለውን ችግርና መከራ በሙሉ ጨርሰው አስወግደውት አሁን የምንኖባት «አገራችን» ዕድልና ድል ሞልቶ የተረፈባት ምድር ትሆን ነበር። እኛ ለዚህ አልተመደብንም፤ አምላክ እኛን የመደበን «እኔ ከሞትሁ ሰርዶ አይብቀል» ያለችውን የአህዮች ፈላስፋ ትምህርትና «ከራስ በላይ ንፋስ» የሚለውን የበሰበሰ የምሳሌ አነጋገር ከወደቀው የኑሮ ስርዓታችን ጋር ደምስሰን «እያንዳንዱ ትውልድ አለምን እሱ በተረከበባት ጊዜ ከነበረችበት ሁኔታ እጅግ የተሻለ አድርጎ ለተተኪው ትውልድ የማስረከብ ኃላፊነት አለበት።» የሚለውንና ብዙ ፈላስፎች የተስማሙበትን ቁም ነገር ፈጽመን አንድ የተሻለችና በእውነት የታደሰች የኢትዮጵያ ልጆች አገር ለትውልዳችን ለማስረከብ ነው። ወያኔ እዚህ ላቀረብሁት አይነት የኢትዮጵያ መፍትሔ ሊሆን አይችልም። ወያኔ አገርን በመዝረፍና ድሀን በመቀማት በጥቅም ጆሮው ስለተዳፈነ ስለኢትዮጵያ መጻኢ እድል የሚበጅን ቅን ሀሳብ መስማት አይችልም።

ከዚህ ላይ በታላቅ ምሳሌነቱ የማንኛውም አገር ሰው የሚጠቅሰውን የአንድ የዓረብ ሽማግሌ ታሪክ ልጠቅሰው እፈልጋለሁ። ታሪኩም የሚከተለው ነው። ዘጠና አመት እድሜ የነበረው አንድ ዓረባዊ ሽማግሌ በጓሮው የተምር ዛፍ ችግኞች በትጋት ይተክላል። አንድ መንገደኛ ይህን ስራ ሲያይ በነገሩ ይደነቅና መንገዱን አቋርጦ ወደ ሠራተኛው ሽማግሌ ሔዶ «በዚህ የርጅና ዘመንህ በማረፍ ፈንታ እነዚህን የተምር ችግኞች በመትከል የምትደክመው መቼ ደርሰውልህ ልትጠቀምባቸው ነው?» ይለዋል። ሽማግሌውም በመንገደኛው ሰውዬ ሞኝነት ስቆ «እኔ ስበላ የኖርሁት ተምር እኔ ሳልሆን አያት ቅድመ አያቶቼ የተከሉት ነው። ከነሱ የወሰድኩትን ዕዳም ለልጅ ልጆቼ መክፈል ስላለብኝ ለነርሱ እተክልላቸዋለሁ» ሲል መለሰ ይባላል።

ሽማግሌው እንዳለው ሁሉ የሰው ጠቅላላ ህይዎት በማያቋርጥ ረጅም ገመድ የተቀጣጠለ በመሆኑ አንድ ትውልድ ላለፉት ትውልዶች ባለ ዕዳ እንደመሆኑ መጠን ለሚተካው ትውልድ አሳሳቢ የሆነ የውለታ ዕዳ ትቶ ማለፍ አለበት። በተለይም እንደኛው ቅድመ አያቶች በሀገሩ ያገኘው ጥቅም ለሀገሩ ካፈሰሰው ላብና ደም በምንም የማይመጣጠን የሆነ ብዙ ስለሌለ ያባቶቻችን ባለዕዳዎች ነን። በዚህ ካላመንና ልክ እንደ ወያኔዎች «የኔ ዕለተ-ምጽዓት እኔ የምሞትበት ዕለት ነው» እያልን ራሳችንን ብቻ የምንወድ ከሆነ በሕይዎት ያለው ምስኪን ኢትዮጵያዊ ወያኔ ህጋዊ ባደረገው የጥላቻ ማንነቶች አጥር ሰርቶ የጋራ ትውስታውን በማጥፋት ርስ በርስ እየተከሳከሰ ጨርሶ ከምድረ ገጽ እስኪጠፋ ድረስ የኢትዮጵያ ምድር የድኩማን፣ የለማኞች፣ የረኃብተኞችና የደንቆሮዎች ሲሆን፤ በሌላም በኩል ኢትዮጵያውያን አባቶቻችን ያቀኗትና አረመኔው ወያኔ የኢትዮጵያውያን የመቃብር ዋሻ ያደረጋት ምድረ ደግሞ የጨቋኞች፣ የዘራፊዎች፣ የቀማኞች፣ የወንጀለኞች አገር እንደሆነች ትቆያለች።

እኛ የዛሬዎቹ የኢትዮጵያ ልጆች ይህንን ጠንቅቀን ተረድተን ለኢትዮጵያ አገራችን ካልደረስንና የህዝባችንን የወደፊት አገር ካላቀናን፤ በተቀነባበረ እቅድ ድኩማን፣ ለማኞች፣ ረኃብተኞችና ደንቆሮዎች ሆነው በወያኔ ጨቋኞች፣ ዘራፊዎች፣ ቀማኞችና ወንጀለኞች ፍዳቸውን እያዩ ኖረው እንዲጠፉ የምንፈርድባቸው ዛሬ የምንወልዳቸውና ከራሳችን በላይ እንወዳቸዋለን የምንላቸው የያንዳንዳችን ልጆች ይሆናሉ። ለየራሳችን ልጆች ደኅንነት ብቻ እንጥራለን ብለን ራሳችንን ብናሞኝ ደግሞ አንድ አይነት ትውፊትና ወግ ያለው ህዝብ አንድ ላይ እንዲሻሻል ካልተደረገ የሐያ አንደኛው መቶ ክፍለ ዘመን ብዙዎቹን በአዘቅት ውስጥ ጥለው ራሳቸው ብቻ በምቾት መፈንጨት ለሚፈልጉ ጥቂት ጮሌዎች ምንም ቦታ የሌላቸው መሆኑን መዘንጋት የለብንም። ለዚህም ምሳሌ ወደሩቅ ቦታ፡ ወደሩቅ ዘመን ሳንሄድ በዓይናችን ያየናቸው ለሀያ አራት አመታት «ሀገራቸውን» በጉድ አዘቅት ውስጥ ጥለው ኑረው በመጨረሻው በራሳቸው ስራ በጉድ አዘቅት ውስጥ የወደቁትንና እየወደቁ ያሉትን ወያኔዎችን ማስታወስ ይበቃል።

እንግዲህ ወያኔ በኢትዮጵያውያን ላይ የሚፈጽመው ደባ ሁሉ ውጤት እንዲህ መሆኑ ከታወቀ ዘንድ፤ የየግል ምኞታችንንና ፍላጎታችንን ከታላቁ ህዝባችን ጠቅላላና ዘላቂ ጥቅም ሳናስቀድም እኛ የኢትዮጵያ ወጣቶች ድርና ማግ ሆነን መስራት ከቻልን እያንዳንዱን ኢትዮጵያዊ ከወያኔ ጥፋት ታድገን የጨለመ ተስፋውን በማለምለም፤ ልጆቹና የልጅ ልጆቹ ተከብረው የሚኖርበት አገር ባለቤት እንዲሆንና የሚኮራበት ርስተ ምድር የመፍጠር ችሎታውም ሆነ አቅሙ አለን። የኢትዮጵያ ልጆች በአንድነት መቆምና በጋራ ለመታገል ቁርጥ ማድረግ፡ ከጅምሩ ጀምሮ «ዘራችን ከዘራቸው፤ ደማችን ከደማቸው ይበልጣል» ብለው ተከታዮቻቸውን ሲጠምቁ የኖሩት ወያኔዎች ለግል ጥቅማቸው ያቋቋሙትንና ህዝባችንን እየፈጁበትና ሀብቱንም እየበዘብዙበት እንዲኖሩ በወንጀል ያቋቋሙትን የሌብነትና የቅሚያ ማህበራቸው የሆነውን «ስመ መንግስት» ገርስሶ፤ ኢትዮጵያውያንን ከጥፋት በመታደግ፤ የሰላም፣ ብልጽግና፣ ፍቅርና የኑሮ ዋስትና የሚገኝበት ኃይል ነው።

በመጨረሻም ሁላችንም ኢትዮጵያውያን መንፈሳዊ መኔውን አግኝተን ይህንን የጋራ የሀሳብ ኃይል መፍጠር ከቻልን ህዝባችንን ከአደጋ ማውጣት ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያን ምድር የምንመካበት አገር ልናደገው ችሎታው አለን። እኔ ዛሬ የሰነቅሁትን እምነት በየቦታው ተበታትኖ ያለው የኢትዮጵያ ምሁር ለኢትዮጵያዊ ወገኑ ለመድረስ በአንድነት ቢገምደው ፕሮፌሰር መስፍን እንዳሉት ኢትዮጵያ በአንድ ትውልድ የአፍሪካ ጃፓን ለመሆን ትችላለች። ግን ጊዜ የለንም፤ በአንድነት ተነቃንቀን የጋራ ኃይላችንን መፍጠር ዛሬ መጀመር አለብን።

ጤና ይስጥልኝ!


Viewing all articles
Browse latest Browse all 8745

Trending Articles