በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አስቴር ማሞ የቦርድ ሰብሳቢነት የሚመራው የፕራይቬታይዜሽንና የመንግስት የልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ ከእስራኤሉ ኤሌኒቶ ኩባንያ ጋር ታንታለምን ለማልማት ድርድር እንዲያደርግ አስቀምጦት የነበረውን አቅጣጫ ውድቅ ማድረጉ ታወቀ።
ኤጀንሲው ከኤሌኒቶን ጋር ታንታለምን ለማልማት የጀመረውን ድርድር እንዲቋረጥ ዋነኛ ምክንያት፣ ኤጀንሲው ያዋቀራቸው የባለሙያዎች የጥናት ቡድን ኤሌኒቶ ታንታለምን ማልማት የማይችል ኩባንያ መሆኑን ባካሄዱት ጥናት በማረጋገጣቸው ነው።
በኤጀንሲው የተሰየመው የባለሙያዎቹ የጥናት ሪፖርት እንደሚያሳየው፣ ኤሌኒቶ ታንታለምን ለማልማት ተገቢው ቴክኖሎጂና የገንዘብ አቅም የሌለው መሆኑን ነው። ኩባንያው 17ሺ ቶን የታንታለም ማዕድን ክምችት አለኝ ቢልም በቦታው በተደረገው ጥናት መረጃው ሐሰት መሆኑ እንዲያውም ምንም አይነት አመላካች ቁፋሮዎች አለማድረጋቸው ተረጋግጧል። ኤሌኒቶ ታንታለምን ለማልማት ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ የመጣ ኩባንያ ቢሆንም ከትክክለኛ መረጃ ውጪ ድጋሚ የማልማት ጥያቄው ተቀባይነት እንዴት ሊያገኝ እንደቻለ የታወቀ ነገር የለም።
የፕራይቬታይዜሽንና የመንግስት የልማት ድርጅቶች ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ወንድአፍራሽ አሰፋ ለሰንደቅ ጋዜጣ እንደገለፁት “ኤሌኒቶ ተገቢውን መስፈርት አሟልቶ ቢሆን ኖሮ እስከአሁን ወደ ስራ ይገባ ነበር። ከዚህ በፊት ታንታለምን በጥሬው ነበር የምንልከው። አሁን እሴት ጨምረን መላክ የማያስችለን ከሆነ ከየትኛውም ኩባንያ ጋር አንደራደርም። እንደውም በራሳችን አቅም ለመስራት ጥናቶች እያደረግን ነው” ብለዋል።
“ታንታለምን ለማልማት የሚያስችል ቴክኖሎጂ በሀገራችን የለም። ይህ በሆነበት ሁኔታ በራሳችን አቅም ሲባል ምን ማለት ነው?” ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ አቶ ወንድአፍራሽ ሲመልሱ፣ “ጥናት እያደረግ ያለነው ስንል የአዋጭነት ጥናት ማለታችን ነው። ከአጋሮች ጋር እንዴት መስራት እንዳለብን እና ሌሎች ማለታችን ነው” ብለዋል።
በዚህ የማዕድን ዘርፍ ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ ለሰንደቅ ጋዜጣ እንደገለፁት፣ “ይህን የታንታለም ልማት መንግስት በግልጽ ሊፈትሸው ይገባል። ላለፉት ሃያ አመታት ዛሬ የኢትዮጵያ ማዕድን ልማት አክሲዮን በተባለ ኩባንያ ታንታለምን በጥሬው ወደ ውጭ ሲላክ መቆየቱ የሚታወቅ ነው። ሀገራችን ካገኘችው ጥቅም የበለጠ ግለሰቦች የከበሩበት ሁኔታ ስለመኖሩ ፀሃይ የሞቀው እውነት ነው። ሌላው ቢቀር ታንታለም የተለያዩ ማዕድናት ውቅቅር ማዕድን (alloy) መሆኑ እየታወቀ ለገበያ በጨረታ ወይም በቀጥታ ሽያጭ ሲደረግ በውስጡ ለያዛቸው ንጥረ ነገሮች ዋጋ እንኳን አይወጣላቸውም። በተቋሙ ውስጥ በመንግስት የተሾሙ ኃላፊዎች ቢኖሩም፣ በጥሬው ማዕድኑ እንዲወጣ እየተደረገ በሌሎች ሀገሮች ውቅሩን ማዕድን ለመለየት በሚከናወን ሂደት ተጠቃሚ በመሆናቸው ግለሰቦቹ የከበሩበት ሀገር ግን ተገቢውን ጥቅም ያጣችበት ሁኔታዎች ናቸው ያሉት። ከሀገር ውስጥ ወደ ውጭ ሰንሰለት ሰርተው የሃገር ሃብትን ላለፉት ሃያ ዓመታት ቢያንስ ሲዘርፉ ሲያዘርፉ የነበሩ የተቋሙ ሃላፊዎችን በቃችሁ ወደ ልማት እንግባ መባል አለባቸው” ብለዋል።
አያይዘውም፣ ብዙ ሀገሮች ታንታለምን የሚያዩት በአንድ ሀገር ልማት ውስጥ ስትራቴጂክ ማዕድን አድርገው ነው። ምክንያቱም፣ ይህ ማዕድን ካፓሲተሮችን ለመስራት የሚስችል በመሆኑ ነው። ይህም የማዕድኑ ባህሪ ለሞባይል፣ ለዲቪዲ፣ ለኮምፒውተር ሃርድዌር እንዲሁም ለላፕቶብስ መስሪያዎች የሚያገለግል ነው። አንድ ሞባይል በአማካኝ በውስጡ 40 ሚሊ ግራም ከታንታለም የተሰራ ክፍል አለው። እንዲሁም ለሞባይል ለቴሌቪዥን ድምጽ ጥራት መጨመር ቁልፉን ሚና የሚጫወተው የታንታለም ማዕድን ነው። ለሕክምና መሳሪያዎችም ያለው ጠቀሜታም የጎላ ነው። ለምሳሌ በሰው ልጆች ልብ ውስጥ የሚቀበረው አርቴፊሻል መተንፈሻ የሚሰራው ከታንታለም ነው። ከዚያም በላይ በቀላሉ የማይቀልጥ በመሆኑ ለሳተላይት ማምጠቂያ የሚያገለግል ንጥረ ነገር ነው” ብለዋል።
በተጨማሪም ታንታለም ኒዖቢየም፣ ቶሪየም እና ዩራኒየም የተባሉ ማዕድናትን በውስጡ ይይዛል። ከኢትዮጵያ የሚወጣው ታንታለም ለገበያ ሲቀርብ እነዚህን ሶስት ማዕድናት ታሳቢ ባደረገ መልኩ አለመሆኑን የተቋሙን ሰነድ የፈተሸ ማንም ግለሰብ ሊረዳው የሚችል ሐቅ ነው። በአንፃሩ ግን በዓለም ገበያ በጣም የተጣራ አንድ ኪሎ ግራም ታንታለም እስከ 300 ፓውንድ ሲሸጥ መካከለኛ የሆነው ከ100 ፓውንድ በላይ እንደሁኔታው ይሸጣል። ይህ የገበያ መጠን ከሶስቱ ማዕድናት ውጪ መሆኑን ልብ ይሏል። ሌላው ኒዖቢየምና የታንታለም ውህድ የሆነው ኮለታን የተባለው ማዕድን በዓለማችን ከፍተኛ የገበያ ድርሻ ያለው ነው። ይህን ማዕድን ለማውጣት በዲሞክራቲክ ኮንጎ ሪፐብሊክ ውስጥ በእርስ በእርስ ጦርነት የጠፋውን የሰው ልጆች ሕይወት መገመት አደጋች መሆኑን አስረድተዋል።
ባለፉት አምስት የእድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዓመታት ውስጥ የማዕድን ልማት ዘርፍ ከሶስት በመቶ በታች ለልማት የዋለ መሆኑ የመንግስት ሠነድ ያሳያል።
“ይህን ያህል ችግር በዚህ ተቋም አለ ካሉ፤ ከዚህ ችግር ውስጥ ለመውጣት ምን ዓይነት አማራጮች አሉ?” ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ ሲመልሱ፣ “መንግስት በማዕድኑ ዘርፍ ግልፅ አቅጣጫ ማስቀመጥ አለበት። በሀገራችን የሌሉ ቴክኖሎጂዎች ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡበት እና የቴክኖሎጂ ሽግግርን መቀበል የሚችሉ ተቋማትን መጠቀም አለበት። ለምሳሌ ላለፉት ሃያ ዓመታት የኢትዮጵያ ማዕድን ልማት አክሲዮን ኩባንያ ታንታለምን በጥሬው ሲሸጥ ከርሞ፤ መንግስት በግልፅ በሽርክና ለማልማት አማራጭ ሲያቀርብ ተቋሙ በበኩሉ በሀገር ውስጥ ለማልማት እየሰራሁ ነው የሚል አማራጭ ይዞ ሲቀርብ ምን ማለት ነው? ከዚህ በፊት ይህ ተቋም ይህን የማድረግ ዕድል እያለው በአንፃሩ ግን በጥሬው ታንታለምን ሲቸበችብ ከርሞ አሁን ላይ በራሴ ላለማ ነው ሲል ይህ ጥያቄ የግለሰቦች ነው ወይንስ የኢትዮጵያ መንግስት ነው ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው የሚሆነው። ስለዚህም መንግስት በግልፅ መንገድ ታንታለምን ለማልማት የሚመጡ ኩባንያዎችን በመቀበል በጋራ ለመስራት ቁርጠኛ የሆነ አሰራር መከተል አለበት። ከዚህ ውጪ ቢሮክራሲውን አንቀው ለራሳቸው ልማት የሚሰሩ ኃላፊዎችን፤ በቃችሁ ወደልማት ልገባ ነው ሊላቸው ይገባል” ብለዋል።
ከዚህ በፊት ኤሊኒቶ ግሩፕ በአፍሪካ ውስጥ በማንኛውም ሁኔታ በማዕድን ቁፋሮ ስራ ላይ የተሰማራ ኩባንያ አለመሆኑን እና በሽርክና አብሮት የሚሰራውም ኤች ጂ ስትራክ የተባለው የጀርመን ኩባንያም ታንታለምን በዓለም ገበያ ውስጥ በመግዛት የሚታወቅ እንጂ ማዕድን በማንጠር የሚያመርት ኩባንያ አለመሆኑንም መዘገባችን ይታወቃል፡፡
ሌላው ኤሌኒቶ ግሩፕ ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው በእህት ኩባንያ አማካኝነት በማዕድን ሚኒስቴር ስር ለሚገኘው የኢትዮጵያ ጂኦሎጂክ ሰርቬይ ግማሽ ሚሊዮን ብር የሚጠጋ የቁፋሮ ስራ ከሰራ በኋላ፣ ክፈል፣ አትክፈል በሚል ጉዳዩ በህግ ተይዞ እንደሚገኝ ይታወቃል። እስካሁንም ድረስም ለመስሪያቤቱ የተከፈለ ክፍያ የለም።