ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ምሽት ላይ ከዚህ ቤት የሚወጣው ድምፅ በአካባቢው ለረጅም ጊዜ ለኖሩት ጎረቤቶች ያልተለመደ ነበር፡፡ በተለይ ማክሰኞና ሐሙስ ከምሽ ሁለት ሰዓት ጀምሮ የጥቂት ሰዎች ህብረ ዝማሬ ጎልቶ ይሰማል፡፡ አልፎ አልፎ ከእነርሱም በላይ የቴፑ ድምፅ አየሩን ሰንጥቆ ያስገመግማል፡፡ ጎረቤቶቹ እያደር የገባቸው ነገር ቢኖር እነዚህ ሰዎች እምነታቸውን መቀየራቸው ነው፡፡ ዝማሬና ‹ሃሌሉያ› የሚል የአንድ ወንድ ድምፅ ሁሌም ይሰማል፡፡ አልፎ አልፎም ምንነቱን ለመለየት የማይቻል ቋንቋ የሚናገር ሰው ድምፅ የምሽን አየር ሰንጥቆ ወደ አካባቢው ነዋሪዎች ጆሮ ይደርሳል፡፡ ይህ ዕለት ተዕለት ሳያሰልስ እየቀተለ ያለ፣ ነገር ግን አዲስ ክስተት ነው፡፡ ብዙውንጊዜ ተዘግቶየሚነሮው የቆርቆሮ ግቢ የነዋሪዎቹን የምሽ ፕሮግራ አፍኖ ሊያስቀር አልተቻለውም፡፡
እነዚህ ግቢ ውስጥ አንዲት እናትና ሁለት ልጆቻቸው ይኖራሉ፡፡ ወደ አስኪ ገብርኤል በሚወስደው ቀጭን የኮረምኮንች መንገድ የግራ ጠርዝ ላይ ካሉት መኖሪያ ቤቶች አንዱ ነው፡፡ ሴትየዋ ዘወትር ጥቁር ልብስ የሚለብሱ፣ ሀዘን ያደቀቃቸው፣ ዕድሜ የተጫናቸው አይነት ናቸው፡፡ የአካባቢው ነዋሪ ሁሌም ሲያያቸው ከንፈሩን ይመጥላቸዋል፡፡ እኚህ ሴት ከሰው ጋር የመግባባት ችሎታቸው ደካማ ቢሆንም ይህንን ክፍተት ሸፍነው በአካባቢው ቤተሰባቸውን ይወክሉ የነበሩት ባለቤታቸው ነበሩ፡፡
በአንድ የመንግሥት መስሪያ ቤት ውስጥ በንብረት ክፍል ኃላፊነት ይሰሩ የነበሩት እኚህ ግለሰብ በአካባቢው የተከበረና የተወደደ ሰብዕና አላቸው፡፡ በተለይ ሀዘን ሲደርስና የአካባቢው ህብረተሰብ ሊሰበሰብበት የሚገባ ችግር ሲፈጠር ሰውየው ለማስተባበር ግንባር ቀደም ተሰላፊ ናቸው፡፡ ሁለት ሴት ልጆቻቸው ከቤታቸው የማይወጡና የአካባቢው ሰው ብዙም የማያውቃቸው አይነት ናቸው፡፤ ባለቤታቸው ብዙ ጊዜ ከሰው ጋር መሰብሰብ የማይሆንላቸው ግንኙነታቸው ደካማ አይነት ቢሆንም ይህን ቤተሰብ በማህበረሰቡ ውስጥ በመቀላቀልና በመወከል ረገድ ግን የሰውየው ድርሻ ትልቅ ነበር፡፡ በዚህም የቤታቸውን ክፍተት በመሸፈን ለማህበራዊ ግንኙነቱ አለመሻከር ብዙ ጥረዋል፡፡ አሁን ግን በዚህ ቤት ውስጥ እኚህ ሰው የሉም፡፡
ከ6 ወራት በፊት ይህ ዘወትር ሳቅና ደስታ የሞላበት የነበረ ቤት ድንገት የሀዘን ድባብ ወረረው፡፡ ሰውየው ባልተጠበቀ ሁኔታ ሳምንት ባልሞላ ህመም ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፡፡ ይህ ድንገተኛ ህልፈት ለሁለቱ ልጆቻቸውና ለባለቤታቸው ከባድ የሀዘን ሸክም ጣለባቸው፡፡ ወትሮም በሰውየው ኃይል ይንቀሳቀስ የነበረው ቤት ዝምታ ዋጠው፡፡ ያከብራቸውና ይወዳቸው የነበረ የአካባቢው ሰው ለቅሷቸውን አደመቀው፡፡ የቤተሰቡን ሀዘን ለማረሳሳት አራት አምስት ቀን ሰው ከዚህ ግቢ አልጠፋም፡፡ እየዋለ እያደረ ግን ዝምታውና ሀዘኑ ለቤተሰቡ ብቻ ሆኖ ቀረ፡፡ በእርግጥም ይህ ቤተሰብ በታላቅ ሀዘንና የብቸኝነት ፈተና ውስጥ የወደቀበት ጊዜ ሆነ፡፡
የ10 እና የ11ኛ ክፍል ተማሪዎች የሆኑት ሁለቱ እህትማማቾች ልክ እንደ ክፍላቸው ሁሉ የሚለያዩትም በአንድ ዓመት ነው፡፡ ተከታትለው የተወለዱ ናቸውና ልክ እንደ መንታ ነው አስተዳደጋቸው፡፡ ይህ እኩያነታቸውና በተለይ እንደ ጓደኛም እንደ እህትም የማይነጣጠሉ ሆነው መታየታቸው በትምህርት ቤታቸውም ጭምር የተለዩ ሆነው እንዲታዩ አድርጓቸዋል፡፡ ለአባታቸው የነበራቸው ልዩ ፍቅርና ቅርበት በድንገት ሲለዩዋቸው የፈጠረባቸው ሀዘን ከባድ ነበር፡፡ ለሳምንታት ያለማቋረጥ አንብተዋል፡፡ በተለይ የ10ኛ ክፍሏ ወጣት ድንገት በመታመሟ የተነሳ ቤተሰቡ በድጋሚ ለሌላ ለቅሶና ጭንቀት ተዳርጎ ነበር፡፡ ልጅቷ ከፍተኛ የአዕምሮ ጭንቀት ይዟት ስለነበርም ህሊናዋን ሳተች፡፡ መጮህ፣ መቃዠት፣ የአባቷን ስም እየጠራች ማልቀስ፣ ‹‹ሊወስዱኝ ነው›› እያለች መቃተት ውሎና አዳሯ ሆነ፡፡ የአባትየው ሀዘን ገና ባልጠገገበትና የቤተሰቡ እንባ ባልደረቀበት በዚህ ጊዜ፤ የዚህች ልጅ እንዲህ መሆን ተጨማሪ ችግር ሆነ፡፡ እናትየው ወደ ፀበል ሊወስዷት ቢሞክሩም በመጮህና በመንፈራገጥ አስቸገረች፡፡ ሰዎች አንዴ ‹‹የሰው አይን ወግቷት ነው›፣ ሌላ ጊዜ ‹ሰይጣን ለክፏት ነው›፣ ‹የአባቷ መቃብር ላይ ተደፍታ ስታለቅስ ጋኔን ተጠናውቷት ነው› ወዘተ… እያሉ የየራሳቸውን መላምት ቢያስቀምጡም፣ የልጅቷን ችግር የሚቀርፍ መፍትሄ ግን ማግኘት አልቻሉም፡፡
እናትየው ዘወትር ቤተክርስቲያን እየሄዱ ፀበል ይዘው በመምጣት ቤት ውስጥ ሊያጠምቋት ሞክረው የሃሳባቸውን ያህል ጤንነቷ ሊመለስላቸው አልቻለም፡፡ ሁልጊዜም ካህናትን ባገኙ ቁጥር ቤታቸው መጥተው ለታመመች ልጃቸው ፀሎት እንዲያደርጉላት መወትወታቸውና ይህንን ተግባራዊ ማድረጋቸው አልቀረም፡፡ ያም ሆኖ የተገኘ ለውጥ የለም፡፡ በሰዎች ትብብርና እርዳታ ለአንድ ሳምንት ያህል ጸበል ብትጠመቅም የተገኘ ለውጥ ግን አልነበረም፡፡
በዚህ መሀል ነበር የቤተሰቡ ጭንቀት ያሳሰባት አንዲት የትምህርት ቤት ጓደኛቸው፣ ለታላቂቱ አንድ ወንጌላዊ መኖሩንነ መጥቶ ቢፀልይላት ሊሻላት እንደሚችል ለታማሚዋ እህት ያዋየቻት፡፡ የእህቷ እንዲህ ሆኖ መቅረት ከአባቷ ሞት ጋር ተደምሮ ሀዘኗን ያበረታባት እህት ይህቺ ወጣት ያቀረበችላትን ሀሳብ በቸልታ አላየችውም፡፡ ይልቅስ ቤት ድረስ መጥቶ ለዚህች ታማሚ ቢፀልይላት ችግር እንደሌለው ለራሷ አሳምና ፍቃደኝነቷን ለጓደኛዋ ገለፀችላት፡፡ የሁለቱ ሃይማኖት የተለያየ ቢሆንም ነገር ግን በዚህ አይነት የጭንቅ ጊዜ የእግዚአብሔርን ስም ጠርቶ ፈውስ ማምጣት ከቻለ የትኛውም ሃይማኖት ቢሆን ለዚህች ልጅ ለውጥ አልነበረውም፡፡ በዚህ የተነሳም ነው ለእናቷ ሁኔታውን ያዋየቻቸው፡፡
እናት ከጥቂት ማቅማማት በኋላ ከልጄ ችግር የሚብስ የለም ብለው ሃሳቡን ተቀበሉት፡፡ ልጃቸው ድና የየትኛውም እምነት ተከታይ ብትን ግድ የላቸውም ነበር፡፡
የ27 ዓመቱ ‹ወንጌላዊ› ነኝ ባይ ወደዚህ ቤት ለመጀመሪያ ጊዜ የመጣው ከአንድ ጓደኛው ጋር ነው፡፡ የታማሚዋን ታላቅ እህት ካገኛትና ስለጌታ አዳኝነት ከሰበካት በኋላ በእህቷ ላይ ያደረውን ሰይጣን ለማውጣት ፈፅሞ እንደማያዳግተው በመግለፅ ዘወትር ምሽት ላይ እየመጣ ፀሎት እንደሚያደርግላት ነግሮ ነበር የሸኛት፡፡ በሁለተኛው ቀን ነው ወዲዲህ ቤት፣ አንድ ጓደኛውንና መጽሐፍ ቅዱስ ይዞ የመጣው፡፡ ቤት እንደገባ እናትየዋን ተዋውቆ ልጅቷ ወደተኛችበት የመኝታ ክፍል ገባ፡፡
ሰው ማየት የማትፈልገውና ዘወትር በፀጥታ ውስጥ ብቻ መቀመጥ የሚያስደስታት ልጅ ወደ ቤት ተከታትለው የገቡትን ሁለት ወንዶችና እናቷንና እህቷን ካየች በኋላ በብርድ ልብሷ ተሸፍና ፊቷን ወደ ግድግዳ አዙራ ተናች፡፡ ‹‹ይህን የሚያደርገው ሰይጣን ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱሱንና ቃሉን የሚመሰክሩትን ሲያይ ይደበቃል›› በማለት ከተኛችበት እንድትነሳ በኃይለ ቃል ያዘት ጀመረ- ወንጌላዊው፡፡ የተሸፈነችው ልጅ ግን ምንም ሳትናገር ፀጥ ብላ ተኝታለች፡፡ በዚን ዕለት ለሁለት ሰዓታት ያህል ሁለቱም ወንዶች ፀሎት አደረሱ፡፡ የተሸፋፈነችበትን ብርድ ልብስ ገልጠው በታላቅ ድምፅ እየጮኹ ፀለዩላት፡፡ ልጅቷ ይህን ጊዜ እየጮኸችና እየተሳደበች ከቤት እንዲወጡ ትወተውት ነበር፡፡
ወጣቶቹ ፀሎታቸውን እንደጨረሱ እናትና እህትን ቆም አድርገው ስለሃዘንና ስለሰይጣን መከላከል ትኩረት አስተማሯቸው፡፡ በእምነታቸው ኢየሱስን ካልተቀበሉ እንደማይድኑ ጭምር፡፡ ይህ ምልልስ ቀናትን በቀናት ላይ እየደረበ፣ እየተደጋገመ መጣ፡፡ ወንጌላዊው ነኝ ባይ ዘወትር 12 ሰዓት እዚህ ቤት እየመጣ የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት እያስተማረ ለልጅቷም እየፀለየላት ይሄድ ጀመረ፡፡ ቀስ በቀስ ቤተኛ ሆነ፡፡ የተኛችው ልጅ ትንሽ መረጋጋት ሲታይባትና ፀሎት ሲደረግ መጮኋን ስታቆም ጊዜ እናትና እህት ተስፋ እየታያቸው፣ ወጣቱን እያከበሩትና የሚላቸውን ሁሉ እየተቀበሉ መፈፀም ጀመሩ፡፡ በዚህ መልካም ያ ቤተሰብ የዚህን ወጣት ሃይማኖት ተቀበሉ፡፡ ቤቱ ዘወትር ማክሰኞ፣ ሐሙስና እሁድ ምሽት ፀሎት የሚደረግበት ቤት ሆነ፡፡
የአካባቢው ሰው ዘወትር ምሽት ላይ በሚሰማው ጩኸት የበዛበት ድምፅ ቢቸገርም እናት ይህን የሚያደርጉት የታመመች ልጃቸውን ለማዳን ካላቸው ጉጉት የተነሳ መሆኑን ስላወቀ ብዙም አልተቀየማቸውም፡፡ ያም ሆኖ ልጅቷ መጮኋን ብትተውም ሙሉ በሙሉ ጤናዋ ተመልሶ ወደ ትምህርት ቤት መሄድ ግን አልቻለችም፡፡ በዚህ የተነሳም ዘወትር ፀሎት ይካሄድላት ነበር፡፡
ወጣቱ ቀስ በቀስ ቤተኛ ከመሆንም አልፎ ዘወትር ለችግራቸው የሚደርስላቸው፣ በጭንቀታቸው የሚያፅናናቸው፣ ዘወትር ከመጽሐፍ ቅዱስ እየጠቀሰ የሚያበረታቸው በመሆኑ እናት ከቤት እንዲጠፋ አልፈለጉም፡፡ በአንድ ሰርቪስ ውስጥ እንዲኖር ፈቀዱለት፡፡
ይህ ወጣት የአርባ ምንጭ ተወላጅ ነው፡፡ ወደ አዲስ አበባ ከመጣ 6 ዓመታት አልፈውታል፡፡ እንደ መጣ በቅድሚያ ያስጠጉት የሀገሩ ተወላጆች የሆኑ የፕሮቴስታንት እምነት ተከታዮች ናቸው፡፡ በዚህ ሳቢያም ከቀደም እምነቱ ለውጠው የነርሱ ሃይማኖት ተከታይ አደረጉት፡፡ መጽሐፍ ቅዱስም ያስተማሩት እነርሱ ናቸው፡፡ በጥቂት ጊዜያት ውስጥ ሙሉ ጊዜውን እያገለገለ ደህና የእምነቱ አጋፋሪ መሆን ቻለ፡፡ በእነርሱ እርዳታም ህይወቱን ይገፋ ጀመር፡፡ ለብዙ ጊዜ ከእነርሱ ሳይለይ ቆየ፡፡ እየዋለ እያደረ ግን ከሰዎቹ ጋር ሊግባባ አልቻለም፡፡ ከ2 ዓመታት በፊት ለብቻው መኖር ጀመረ፡፡ ህይወት ከበደችው፡፡ በአንድ መስሪያ ቤት ውስጥ በተላካኪነት ተቀጥሮ እንዲሰራ አንድ ቤተክርስቲያን ውስጥ ያውቀው የነበረ ሰው ረዳው፡፡ ቀን ቀን እየሰራ አልፎ አልፎም ቤተክርስቲያን እያገለገለ መኖር ጀመረ፡፡ ያም ሆኖ የቤት ኪራይና የራሱን ምግብ ሸፍኖ መኖር የሚችልበት አቅም አጣ፡፡ በዚህ መሀል ነው ከዚህ ቤተሰብ ጋር የእምነቱ ተከታይ በሆነች አንዲት ተማሪ አማካኝነት መተዋወቅ የቻለው፡፡
ዛሬ የኑሮ ሸክሙን ሊያቃልልለት የቻለ አጋጣሚ ተፈጥሮለታል፡፡ በዚህ ግቢ ውስጥ ቤት ተሰጥቶት መኖር ጀምሯል፡፡ ምግቡም ከዚሁ ነው፡፡ ዘወትር የፀሎት ፕሮግራም እያካሄደ ለዚህ ቤተሰብ የሚሰጠውን አገልግሎት ላለማቋረጥ ይተጋል፡፡ ባህሪው ግን ከዚህ ቀደም ከነበረበት እየተበላሸ መጥቷል፡፡ ልጁ መጠት ለምዷል፡፡
ከቤተክርስቲንና ከቀድሞ ክርስቲያን ጓደኞቹ እየራቀ በመጣ ቁጥር በዚያው መጠን መስሪያ ቤት ከተዋወቃቸው ጓደኞቹ ጋር መንጎዳጎድ ጀመረ፡፡ አንድ ሁለት በማለት የተጀመረው መጠት የእምነቱን ምሰሶ ናደበት፡፡ ወንጌላዊ ነኝ ቢልም በምግባሩ ግን ከዕምነቱ ፈቀቅ አለ፡፡ ላለፉት ስድስት ዓመታት በፅናት የኖረበትን ህይወት ረሳው፡፡ ያም ሆኖ ግን የሚኖርበት ቤተሰብ ይህን እንዳያውቅ በጣም ይጠነቀቃል፡፡
እየዋለ እያደረ ሲሄድ ሰይጣናዊ ሃሳብ በአእምሮው ተሰነቀረበት፡፡ ከሁለቱ ልጆች ጋር የነበረው ግንኙነት ከወንድማዊ ስሜት እየወጣና በፆታዊ ፍላጎት እየተተካ መጣ፡፡ በተለይ ታማሚ የሆነችውንና ዘወትር ፀሎት የሚደረግላትን የ18 ዓመት ወጣት በልዩ አይን ያያት ጀመር፡፡ ፀሎት በሚያደርግላት ጊዜ ሁሉ የሚነካካውን የሰውነት ክፍሏን በፆታዊ ምኞት ያየው ጀመር፡፡ የፍላጎቱን ለመፈፀምም ብልሃት መፍጠር ጀመረ፡፡
አንድ ምሽ ድራፍት ጠጥቶ መጣ፡፡ በተቻለው መጠን መጠጥ መቅመሱን እንዳያውቁበት ጥንቃቄ ያደርጋል፡፡ እንዳይሸትበትም የተለያዩ ዘዴዎችን ይጠቀማል፡፡ ቤተሰቡ እንደ ወንድም ያየው ስለነበርም ያከብረዋል፡፡ ቤት እንደገባ የ18 ዓመቷ ወጣት መኖርና አለመኖሯን ጠየቀ፡፡ እንደተለመደው መኝታ ቤቷ መሆኗን ነገሩት፡፡ እሱ ፀሎት በሚያደርግላት ጊዜ ማንም ወደዚህ ቤት አይገባም፡፡ እናትየው ያለመሰልቸት ለሚያደርግላት የፀሎት እርዳታ ያመሰግኑታል፡፡ ቤተሰቡ በእርግጥም ተሰላችቷል፡፡ ሚያዝያ 14 ቀን 1999 ዓ.ም ከምሽ 2፡00 ሰዓት፡፡
በሩን ከውስጥ ቀረቀረው፡፡ መጽሐፍ ቅዱሱን አወጣ፡፡ ልጅቷ ስታየው በፈገግታ ተቀበለችው፡፡ ታከብረዋለች፡፡ ችግሯንም ታዋየዋለች፡፡ ብቸኝነት መፈለጓን ነው ዘወትር የምትነግረው፡፡ ዛሬ የሚያደርጉት ፀሎት የተለየ መሆኑን ነገራት፡፡ በመንፈስ ተመርቶ መምጣቱን ነበር የገለፀላት፡፡ ‹‹የምትፈወሽበት ወቅት ደርሷል፡፡ አሁን ከሰይጣን እስር ነፃ ትወጫለሽ›› አላት፡፡ ልብሶቿን በሙሉ እንድታወልቅና በፊቱ እንድትቆም ነገራተ፡፡ የተባለችውን አደረገች- ከጡት መያዣዋና ከውስጥ ሱሪዋ በቀር ሙሉ በሙሉ ራቁቷን ከፊቱ ቆማለች፡፡ አይኗን እንድትጨፍን አዘዛትና ፀሎት ጀመሩ፡፡ ከጥቂት ቆይታዎች በኋላ ፈፅሞ በማይታወቅ ቋንቋ መጮህ ጀመረ፡፡ ጆሮዋን ይዞ እሷ ባልገባት ቋንቋ ለርሱ ግን ‹በመንፈስ ቅዱስ ቋንቋ› መለፍለፍ ጀመረ፡፡ ጆሮዋ ላይ ይለፈልፍ ስለነበርም ልጅቷ እየተጨነቀችና እየቃተተች መጣች፡፡ ገፋ አደረገና አልጋው ላይ በጀርባዋ አጋደማት፡፡ ንግግሩን ሳያቋርጥና አይኗን እንዳትገልጥ አዝዞ የጡት ማስያዣዋን አወለቀው፡፡ ጡቷን ነከሳት፡፡ ለመጮህ ሞከረች፡፡ አፏን በእጆቿ ግጥም አድርጎ ያዘው፡፡ አፉ አልኮል አልፎክ ሸተታት፡፡ በዚህ መሀል ሳታውቀው የውስጥ ሱሪዋን አውልቆ ደፈራት፡፡ የምታስታውሰው ለመጨረሻ ጊዜ በህመም መጮኋን ነበረ፡፡
ሁለት ቀናት አለፉ፡፡ ከዚያ በኋላ አንሶላ ላይ የፈሰውን ደም ራሷ ናት ያጠበችው፡፡ የሆነችውን ነገር ያወቀ ሰው አልነበረም፡፡ ከዚያን ቀን ጀምሮ ያመጣችው አዲስ ፀባይ ማልቀስ ብቻ ሆነ፡፡ ‹‹ለመዳን ያለሽ ዕድል ይህ ነው- ያንቺ ሰይጣን መውጣት የሚችለው በዚህ መልክ መሆኑን በራዕይ ነግሮኛል›› ብሎ አስፈራርቷታል፡፡ ለሰው ይህን ምስጢር እስከ ህይወቷ መጨረሻ እንዳታወጣም አዝዟታል፡፡ ይህን ጥቃቷን በልቧ ደብቃ ዝም አለች፡፡ ከዚያ በኋላ ሁለት ጊዜ ተመሳሳይ ነገር ፈፅሞባታል፡፡
ከ2 ወራት በኋላ የዚህ ሰው እኩይ ተግባር ወደ ታላቅየዋ ዞረ፡፡ ባላሰበችው ሁኔታ ዘወትር ያደንቃታል፡፡ መንፈስ ቅዱስ የእህትሽን መዳኛ ነግሮኛል ይላትም ነበር፡፡ አንድ ቀን አስቀምጦ ያሰበውን ሁሉ ነገራት፡፡ የርሷ ድንግልና ውስጥ የተደበቀ ሰይጣን እህቷን እያሰቃያት እንደሆነና ይህን ሰይጣን ከሰው ጋር ተገናኝታ ካላወጣችው በቀር እህቷ ልትሞት እንደምትችል ነገራት፡፡ ደነገጠች፡፡ ፈፅሞ እሱን አልጠረጠረችውም፡፡ ከዚያን ዕለት ጀምሮ ይህቺ ልጅ ሌላ ጭንቀት ተፈጠረባት፡፡ እህቷ ዘወትር ስታለቅስ ስታያት በእርግጥም ልትሞት እንደምትችል አሰበች፡፡ ይህን ወሬ በተደጋጋሚ ነግሯት ሲያበቃ አንድ ምሽት እርሱ ራሱ በመንፈስ ቋንቋ እየለፈለፈ ከርሷ ጋር ሊገናኝ እንደሆነ በአማርኛ አወራላት፡፡ ደነገጠች፡፡ ብቻዋን በነበረችበት ወቅት ስለነበር ይህን ለመቃወም ዕድል አልነበራትም፡፡ በኋይል አቀፋት፡፡ ልትታገለው ሞከረች፡፡ ሙሉ በሙሉ መለወጡን ለመራት አልተቸገረችም፡፡ እምቢ ብትል እህቷ ልትሞት መሆኑን አወቀች፡፡ ምርጫ አልነበራትም የፈቀደውን እንዲያደርግ ራሷን ሰጠችው፡፡
ወንጌላዊ ነኝ ባዩ ወጣት የሁለቱን እህትማማቾች ክብር ገሰሰ፡፡ ከሁለቱም ጋር ባስፈለገው ሰዓት ወሲብ ይፈፅም ጀመር፡፡ እያስፈራራና በሰይጣን እያሳበበ የሰይጣን ስራም ይሰራ ነበር፡፡ ይህን ምስጢር ማንም የሚያውቅ የለም፡፡ የሁለት ልጆቻቸው ባህሪ መለዋወጥና ብቸኝነትን መሻት ግራ ያጋባቸው እናት ሁሉንም ነገር በርሱ ላይ ጥለውታል፡፡ ሶስት ወራት ሲያልፍ ግን የ18 ዓመቷ ወጣት መፀነሷን አወቀች፡፡ የወር አበባዋ ቀረ፡፡ ጭንቀቷ በረከተ፡፡ ይህም ነገረችው፡፡ እርሱም ሊሆን እንደማይችል ነግሮ ሽንቷን የምትመረምርበት የእርግዝና ማረጋገጫ ገዝቶ አመጣላት፡፡ በእርግጥም እርጉዝ ነበረች፡፡ ብዙም የደነገጠ አይመስልም፡፡ በቅርብ ቀን አንድ ሐኪም ቤት ወስዶ እንደሚያስወጣላት ነገራት፡፡ ይሄኔ ነበር ልጅቷ ይህ ወጣት በነፍሷ እየተጫወተ መሆኑን የተረዳችው፡፡ ከባድ ጭንቀት ውስጥ ወደቀች፡፡
አንድ ምሽ እንደተለመደው እህቷ ከትምህርት ቤት ስትመጣ ልታያት ፈልጋ እናቷን ጠየቀች፡፡ ሐምሌ 3 ቀን 1999፡፡ እናትየው ከቀን ጀምሮ በሯን ዘግታ መኝታ ቤት ውስጥ ገብታ እንደቀረችና ከዚያ በፊት ግን አድርጋ በማታውቀው ሁኔታ ሳሎን መጥታ ከርሳቸው ጋር ተጫውታ እንደምትወዳቸው ነግራቸውና ስማቸው መሄዷን ነገሯት፡፡ ‹‹እየዳነች ነው፡፡ አልረብሻትም፡፡ ብያታለሁ ትተኛ›› ነበር ያሏት፡፡ ታላቅ እህት ግን ደስታ አልተሰማትም፡፡ ‹የተሻላትን እህቷን› ልታያት ተመኘች፡፡ በሩን አንኳኳች፡፡ መልስ የለም፡፡ ደጋገመች ዝምታ በዛ፡፡ እየተጠራጠሩ መጡ፡፡ በሩን በተደጋጋሚ ጊዜ ቢደበድቡትም ምላሽ የሚሰጣቸው ሲያጡ ጊዜ በብረት መፈልቀቅ ጀመሩ፡፡ ታግለው ሰበሩት፡፡ ውስጡ ገቡ፡፡ ያዩት ነገር ግን ፈጽሞ ያላሰቡት ሆነ፡፡ ልጅቷ የጣራውን የኮርኒስ እንጨት በስታ ባንጠለጠለችው ነጠላ ታንቃ አገኟት፡፡ ህይወቷ አልፏል፡፡ ከዚህ በኋላ ጩኸት ብቻ ነበር ለአካባቢው የተረፈው፡፡ የሰፈሩ ሰው ተሰበሰበ፡፡
ፖሊስ አስከሬኑን ሲያነሳ አልጋ ላይ ባለመስመር ወረቀት ተፅፎ የተቀመጠ ‹‹ለእህቴ›› የሚል ደብዳቤ አገኘ፡፡ ይህ ደብዳ የልጅቷን የመሞት ምስጢር አጋለጠ፡፡ ወጣቷ ለእህቷ በፃፈችው ደብዳቤ ላይ ‹ወንጌላዊው› ያደረጋትንና በዚህ ሳቢያ መፀነሷን ይህን ጭንቀት መቋቋም ባለመቻሏም ህይወቷን ማጥፋት አማራጭ አድርጋ መውሰዷን ገልፃለች፡፡ ፖሊስ ይህን ደብዳቤ ይዞ ምሽት ላይ አብሮ ያለቅስ የነበረውን ‹ወንጌላዊ› በቁጥጥር ስር አዋለው፡፡ ይህ የተገለጠ ምስጢርም እህትየዋን አነቃት፡፡ የሆነችውን ሁሉ ለፖሊስ ተናገረች፡፡ ወጣቱ እስር ቤት ገባ፡፡
እናት የባላቸው ሞት ሀዘን ሳይለቃቸው ገና የልጃቸውን ህይወት ለማትረፍ ገብቶ ነፍሷን የቀማቸውን ሰይጣን አጠገባቸው አስቀምጠው ኖሩ፡፡ በዚህም የሚወዷትን ልጃቸውን አጡ፡፡ ሌላኛዋ ልጃቸውም ለእህቷ ስትል ክብረንፅህናዋን ያለፍላጎቷ ማጣቷ አንገበገባቸው፡፡ በሀዘን ደቀቁ፡፡ ‹ወንጌላዊው› የሰራውን ሃጢአት በሙሉ ተናዘዘ፡፡ የልጆቹ ውበት ስጋዊ ፍላጎቱን ማነሳሳቱንና ሃጢአት መፈፀሙን አመነ፡፡ ቀድሞ ግን ከሁለቱም ጋር ወሲብ የፈፀመው በራሳቸው ፍላጎት መሆኑን ገልፆ ነበር፡፡ ቆይቶ ፀፀት ሲያንገላታው ነው እውነቱን የተናገረው፡፡
ጉዳዩ የብዙዎችን ቁጣ ቀስቅሶ ነበር፡፡ ወጣቱም በተደራራቢ ክስ ነበር ፍርድ ቤት የቀረበው፡፡ ፖሊስ ሀሰተኛው ወንጌላዊ ብሎ የሰራውን ስራ ለመገናኛ ብዙሃን ገልፆበታል፡፡ በዓለም ለእስር፣ በሰማይ ደግሞ ለሲዖል የሚዳርገውን ሃጢአት ሰርቷልና እስኪያልፍ ድረስ መኖሪያው በእስር ቤት ሊሆን ግድ ሆነ፡፡ የፀፀት አለንጋ ይሸነቁተው ይሆናል፡፡ ምናልባትም የዚያች በሽተኛ ወጣት ድምፅ ይረብሸው ይሆናል፡፡ ከሁሉ በላይ ግን ብቸኝነት የነገሰበትን ቤተሰብ ለቀዘቀዘና ለባስ ብቸኝነት ዳርጎ ሄዷል፡፡