(ዘ-ሐበሻ) የኢትዮጵያ አዲስ አመትን በማስመልከት 4 ዝነኛ ድምፃውያን የሙዚቃ አልበሞቻቸውን እንደሚለቁ ለዘ-ሐበሻ የደረሰው መረጃ አመለከተ። እንደመረጃው ከሆነ ምንም እንኳ በአሁኑ ወቅት ለአንድ ድምጻዊ ሶሻል ሚድያ፣ ብሉ ቱዝ፣ ፍላሽ ድራይቭ እያሉ ሲዲ አውጥቶ ሸጦ ለማትረፍ የማይታሰብ ቢሆንም ይህንን ተቋቁመው ድምጽውያኑ ሥራዎቻቸውን ይለቃሉ።
ለረዥም አመታት የሙዚቃ አልበሞችን ሳይሰራ የዘለቀው ኤፍሬም ታምሩ የድሮ ዘፈኖቹን በድጋሚ በኮሌክሽን መልክ ሰርቶ ያጠናቀቀ ሲሆን በነሐሴ ወር መጨረሻ ላይ ይለቀቃል ተብሎ ይጠበቃል። የኤፍሬምን አልበም የሚያሳትመው ኤሌክትራ ሙዚቃ ቤት ሲሆን ኤልክትራ ከወራት በፊት የወጣውን የአስቴር አወቀ ሲዲ ሳያሳትም ቀርቶ በራሷ መንገድ እንዳወጣችው ይታወሳል። እንደ ምንጮች ገለጻ የአስቴር የመጨረሻው አልበሟ በጣም የተሰማላት ቢሆንም በሽያጭ በኩል ግን አይደለም። አብዛኛው ሰው በሶሻል ሚድያ፣ በኮፒና ዘመኑ ባፈራቸው ቴክኖሎጂዎች በመከፋፈል ድምጻዊቷን አክስሯታል።
ከኤፍሬም በተጨማሪ በናሆም ሪከርስ በኩል አልበሙን የሚለቀው ታምራት ደስታ ሲሆን፤ በአብ ኢንተርቴይመንት በኩል ደግሞ አብነት አጎናፍር አዳዲስ ሥራዎቹን ይዞ ይቀርባል። በሌላ በኩልም በሰላም ሪከርድስ አማካኝነት ዮሴፍ ገብሬ (ጆሲ ኢን ዘ ሐውስ) አዲሱን የሙዚቃ አልበሙን በአዲስ አመት ይለቃል ተብሎ ይጠበቃል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ቴዲ አፍሮ “ሰባ ደረጃ” የሚል አዲስ ነጠላ ዜማ በቅርብ ቀን እንደሚለቅ ለቴዲ ቅርብ የሆኑ ወገኖች ለዘ-ሐበሻ ገልጸዋል።