![Dede Tirs]()
ማለዳ ወደ ሥራ ለመምጣት በገባሁበት ታክሲ ውስጥ ነው ከፊቴ የተቀመጡት ሁለት ጓደኛሞች የሚነጋገሩት ነገር ጆሮዬ ውስጥ የገባው። «ጥርሶቼ ደህና ሆነው ድዴን ያመኛል ስፍቀው በጣም ይደማል ምን ይሻለኛል?» ትላለች የመጀመሪያዋ «በሎሚ እሺው ይተውሻል ጥርስሽ ደህና ከሆነ ችግር የለውም» የሚል መልስ ሰጠቻት አብራት ያለች የዕደሜ አቻዋ። የእነርሱን ወሬ ተወት አድርጌ ወደ ራሴ ሃሳብ ገባሁ። «እውነት የድድ ህመም በቀላል የምናየው ነው ወይስ ከባድ በሽታ?» ስል አሰብኩ። የዚህን ጥያቄ መልስ ለማግኘት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጥርስ ህክምና ማዕከል ውስጥ የማስተማርና የህክምና አገልግሎት የሚሰጡትን ዶክተር ባንቺአምላክ ደምሴ ለማግኘት ቀጠሮ ያዝኩ።
ረዳት ፕሮፌሰር ዶክተር ባንቺአምላክ የፊትና የአገጭ ቀዶ ህክምና ስፔሻሊስትና መምህርት ናቸው። ስለተነሳሁበት ጉዳይ ሙያዊ ማብራሪያ ሰጥተውኛልና ላካፍላችሁ ወደድኩ። ለቃለምልሱ ፈቃደኛ ስለሆኑና እውቀታቸውን ስላካፈሉን ምስጋናዬ በቅድሚያ ይድረሳቸው።
– የድድ ህመም ምንድንነው? መንስኤውስ?
ዶክተር ባንቺአምላክ፦ የድድ ህመም ሲባል የአንድ በሽታ ስም ቢመስልም የተለያየ ዓይነት የድድ ህመሞች አሉ። አንደኛው በኢንፌክሽን ምክንያት የሚመጣ ማለትም በምንበላው ምግብ የተነሳ የመቆጣት ህመም ሲሆን፤ ሌላው ደግሞ በእባጭ መልክ የሚመጣ ከጥርስ ጋር በተያያዘ ከዕጢ ወይም ከካንሰር ጋር በተያያዘ የሚመጣ የድድ ህመም ነው። ሌላው ከሰውነታችን የጤንነት ጉድለት ማለትም በቪታሚን ሲ እጥረት ምክንያት በስኳር በሽታና ሌሎች የጤና ችግሮች ሳቢያ ሊመጣ የሚችል ነው። በዋናነት በእድገት አለመስተካከል ማለትም ጥርስ እድገቱን ሳይጨርስ ውስጥ ሲቀር የሚከሰተውና በጥርስ ንፅህና ጉድለት የሚመጡት ናቸው። በተለይ ደግሞ በጥርስ ንፅሀና ጉድለት የሚከሰተው ህመም በአብዛኛው የሀገራችን ታማሚዎች ችግር ነው።
አዲስ ዘመን፦ ህመሙ የሚያመጣው ጉዳት እንዴት ይገለጻል?
ዶክተር ባንቺአምላክ፦ በጥርስ ንፅህና ጉድለት የሚመጣው በሽታ የድድ መሸሽ እና ድድ አቅም አጥቶ ጥርስ በራሱ ጊዜ እንዲወልቅ ያደርጋል፡፡ ሌላው ደግሞ እንደየ ህመሙ ዓይነት የተለያዩ ጉዳቶችን በማድረስ የነርቭ ችግር እስከማምጣት ብሎም እስከሞት የሚያደርሱ የድድ ህመሞች መገለጫዎች ናቸው።
ይሄን ችግር ለመከላከል ምን መደረግ አለበት?
ዶክተር ባንቺአምላክ፦ የሀገራችን ዋንኛ ችግር የሆነውን በፅዳት ጉድለት የሚመጣ የጥርስ ህመም በአግባቡ በማፅዳት ብቻ መከላከል ይቻላል። ይህም ሲባል በመጀመሪያ ደረጃ በመጉመጥመጥ፣ በመፋቂያ በመፋቅ ማስወገድ ይቻላል፡፡ አንዳንዴም እየተመገብናቸው ቆጠሻሻን የሚያስወግዱ የምግብ ዓይነቶች ማለትም እንደ ሸንኮራ፣ ኮክ፣ ካሮት የመሳሰሉትን በማኘክ ማፅዳት ይቻላል። ሌላው በጥርስ ሳሙና መቦረሽ ፅዳትን ይፈጥራል።
ሌሎቹን ዓይነት ህመሞችንስ በምን መከላከል እንችላለን?
ዶክተር ባንቺ አምላክ፦ ሌሎቹን ማለትም በተለያዩ ህመሞች ምክንያት የሚመጡትን መከላከል በጣም ከባድ ነው። ለምሳሌ ኤች. አይ.ቪ ህመም ያለባቸው ሰዎች ድዳቸው የማበጥ ችግር ያመጣል፡፡ ለተለያዩ ዓይነት በሽታዎች የሚወሰዷቸው መድኃኒቶችም ድድን ሊያሳብጡ ይችላሉ። በእርግዝና ወቅት የሚመጡ የድድ ህመሞች አሉ። እነዚህን በህክምና ለማስወገድ መሞከርና በራሳቸው ጊዜ ሊተዉ የሚችሉ ከመሆናቸው በቀር ይህ ቢደረግ ይተዋል የሚባል ነገር አይኖርም።
ድድ ራሱ አብጦ ራሱ ይጎድላል ይሄስ ህመም ነው ወይስ ሌላ የጤና ችግር?
ዶክተር ባንቺአምላክ፦ ይህ ችግር የሚመጣው «ሸሄላ» ማለትም ምግብ በጥርስ ውስጡ ተጠራቅሞ በሚጠነክርበት ጊዜ በድድ ውስጥ ስር ሰዶ ድዱ እንዲቆጣና እንዲደማ ሲያደርገው ነው፡፡ ይሄ ጥርስ እየተፀዳም ቢሆን በአጸዳድ ጉድለት ሊመጣ ይችላል፡፡ በነገራችን ላይ በጥርስ ህክምና ታሪክ እንደ ድድ ህመም ከባድና አስቸጋሪ ሁኔታ የለም። ድድን ማዳን ከባድ ነው። ጥርሱን አቃፊ አልባ ሊያደርግ የሚችል ጉዳት ያደርሳል።
ድድ የማበጥ ችግር እንዳ ይከሰትበ ት ምን መደረግ አለበት?
ዶክተር ባንቺ አምላክ፦ ችግሩ እንዳይመጣ መንስኤውን ማቆም ዋናው መፍትሔ ነው። በበሽታ ምክንያት የሚመጣውንም የድድ ህመም በመታከም በትክክለኛ አፋፋቅ በማፅዳት የጥርስ ህመምን ማስወገድ ይኖርብናል። ንፁህ ጥርስ እንዲኖረንም ቢያነስ በቀን ሁለቴ ማለትም ጠዋት ቁርስ ከተበላ በኋላና ማታ ወደ መኝታ ከመኬዱ በፊት ጥርስ መፋቅ አለበት። ውሃ መጉመጥመጥም ለጥርስ ንፅህና ይረዳል።
ጥርስ ሲፋቅ ቢያንስ ለ5 ደቂቃ ያህል በትዕግስት መፋቅ አለበት። ይህም ከቀኝ የላይኛው የጥርስ ክፍል እየተፋቀ ወደ ግራ ከግራ ደግሞ ወደታችኛው የጥርስ ክፍል ከዚያ ደግሞ ወደቀኝ በማድረግ ውስጡንና ምላስንም በጥንቃቄና በተገቢው መንገድ ማፅዳት ያስፈልጋል።
የድድ ህክምናስ እንዴት ይካሄዳል?
ዶክተር ባንቺ፦ ህክምናው በንፅህና ጉድለት የሚመጣውን በንፅህና ከመከላከል ባሻገር ህክምናው የተጋገረ ቆሻሻ ካለ በእጥበት ማስወገድ፣ የተጎዳ ጥርስ ካለ በሙሌት ማከም ወይንም መንቀል፣ ድድ በተለያዩ መድኃኒቶች እንዲድን ማድረግና እስከ ቀዶ ህክምና የሚደርሱ የህክምና ዓይነቶች አሉት።
የጥርስ ሳሙና መጠቀም አፍ ያሸታል የሚባለውስ ነገር ምን ያህል እውነት ነው?
ዶክተር ባንቺአምላክ፦ አዎ ብዙ ሰው አፍ ያሸታል ሲል ይደመጣል። የጥርስ ብሩሽ በመጠቀም አፍ ያሸታል የሚባለው ነገር ግን ከእውነት የራቀ ነው። እንዲያውም በተቃራኒው ለአፍ ጥሩ ጠረን በመስጠት ጥሩ ስሜት እንዲሰማን ያደርጋል። ማንኛውም የጥርስ ሳሙና የማፅዳት፣ የአፍ ጠረንን የማሳመር አቅም አለው፣ ተዋስያንን የመግደል ብቃትም አለው፣ ፍሎራይድ የያዘ ስለሚሆን መጠቀሙ ምንም ጉዳት አይኖረውም።
በአጋጣሚ አለርጂክ ኖሯቸው የድድ መቆጣትና ሌላ ችግር እንዳይገጥማቸው የሚመቻቸውን መምረጥ የተጠቃሚዎች ፈንታ ነው። አፍ ያሸታል የሚባለው ነገር የሚመጣው እኔ ሲመስለኝ ንፅህናውን ተለማምደው ሲተውት የሚከተለው የቆሻሻውን የመለየት ሂደት ሊሆን ይችላል።
የምንጠቀመውሰ የጥርስ ብሩሽ ለምን ያህል ጊዜ ያገለግላል?
ዶክተር ባንቺ አምላክ፦ በአብዛኛው የጥርስ ብሩሽ አጠቃቀም ላይ ችግሮች ይስተዋላሉ። የምንጠቀመው የጥርስ ብሩሽ የእጅ መያዣው ወደታች ብሩሹን ወደላይ በማድረግ አየር እንዲያገኝ ማድረግ ይቻላል። በየሦስት ወሩ በመቀየር ጤናው በተጠበቀ ብሩሽ ጥርስን ማፅዳት ተገቢ ነው።
የጥርስ ሳሙና በራሱ የጣፋጭነት ጣዕም ስላለው ጣፋጭነቱ ጥርስን አይጎዳም ወይ?
ዶክተር ባንቺ አምላክ፦ የጥርስ ሳሙናዎች ሲዘጋጁ ጣዕም ለማሳመር የሚደረጉ ፍሌቨሮች ካልሆኑ በስተቀር ጥርስን የሚጎዳ ምንም ነገር አይኖረውም፡፡ ይህማ ከሆነ የተነሱለትን ዓላማ ዘነጉ ማለት ነው። የጥርስ ሳሙናዎች ጥርስ የማጠንከር የአፍ ጠረንን የማሳመርና የማፅዳት አቅም ነው ያሏቸው።
በአጠቃላይ በድድ ላይ ያሉትን ህመሞች ከማከም በላይ ለሁሉም ቢያንስ በቀን ሁለቴ ማፅዳት፣ ጥርስ ስለታመመ ብቻ ሳይሆን በየጊዜው እየሄዱ የጥርሱ ህመም ምን ደረጃ ላይ እንዳለ ማሳየት፣ ከመታመሙና ችግር ከመፈጠሩ በፊት መከላከል ያስችላል።
ጸሐፊ አስመረት ብስራት